የሰውነትዎን ቆዳ ልስላሴና ጤንነት በመጠበቅ የወጣትነት ገጽታዎን ባለበት ማቆየት ይችላሉ።
የስነ ውበት ባለሙያዎች ደግሞ ለመልካም የሰውነት ገጽታ የሚረዳውን የቆዳዎን ጤንነት ለመጠበቅ እና የቆዳ መሸብሸብን ለማስወገድ እነዚህን መንገዶች ይከተሉ ይላሉ።
አብዝቶ የፀሃይ ብርሃን አለመመታትና ሰውነትን ለፀሃይ ጨረር አለማጋለጥ፤
ሲጋራ አለማጨስ፦ የቆዳ መሸብሸብ የሚያጨሱ ሰዎች ላይ ይከሰታል፤
በሃኪም የሚመከሩ የሰውነት ቆዳ ላይ ቅባቶችን በመጠቀም ቆዳን ማለስለስ፤
በጀርባ መተኛትን ማዘውተር፦ በጎንዎ አልያም በፊትዎ ተደፍተው የሚተኙ ከሆነ አንሶላውና ብርድ ልብሶች ሰውነትዎ ላይ መስመር ያወጣሉ።
በጎንዎ መተኛትን ሲዘወትሩ ደግሞ በጭን እና በጉንጭ አካባቢ የቆዳ ላይ መስመሮችን በማውጣት በሂደት የቆዳ ላይ መሸብሸብን ያስከትላል፤ በፊትዎ መተኛት ደግሞ በጭራሽ አይመከርም።
አሳን አዘውትሮ መመገብ፦ አሳ በተፈጥሮው የፕሮቲን ምንጭ በመሆኑ ለቆዳ ደህንነት እና ጤናማነት እጅጉን ይረዳል።
ከዚህ ባለፈም በውስጡ ያለው ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ የቆዳን ውበት ጠብቆ ለማቆየትና የወጣትነት ገጽታን ለማላበስ ይረዳል።
ይህ ንጥረ ነገር የቆዳ መሸብሸብ ሰውነት ላይ እንዳይከሰትም ያደርጋል።
ፊትን ከመጠን በላይ አለመታጠብ፦ ፊትን መታጠብ እና ማጽዳት ተገቢ ቢሆንም ከመጠን በላይ መታጠብና ማጽዳት ግን ጉዳት እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በዚህ መልኩ አብዝቶ መታጠቡ ቆዳችን ራሱን መከላከል የሚችልበትን ቅባት በማስወገድ ድርቀትን ያመጣል።
ይህ እንዳይሆን ደግሞ ቅባታማ በሆኑ የፊት መታጠቢያ ሳሙናዎች መታብን ያዘውትሩ፤ ከዚህ ባለፈም የፊት ቅባቶችን ይጠቀሙ።
ቪታሚን ሲ፦ ቪታሚን ሲ ያለባቸውን ምግቦች መመገብና ማዘውተርም ሌላው የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ነው።
ቪታሚን ሲ በተፈጥሮው የቆዳ ላይ ድርቀተን መከላከልና ማስወገድ ይችላል።
ከዚህ ባለፈም አላስፈላጊ የቆዳ ላይ መስመሮችንና ምልክቶችን ለማስወገድና የቆዳ ላይ ጉዳትን ለመቀነሰም ይረዳል።
አኩሪ አተር፦ አኩሪ አተርን በምግብነት ሳይሆን የተፈጨውን ዱቄት በውሃ አርሶ ቆዳ ላይ በመቀባት፤
አልያም ደግሞ የአኩሪ አተሩን ዘይት ሰውነትን ከታጠቡ በኋላ መቀባት መልካም መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ይህን ሲያደርጉ በከፍተኛ የፀሃይ ጨረር የተጎዳን የሰውነት ቆዳ እንዲያገግም ያደርጋል፣ የቆዳን ተፈጥሯዊ ወዝና ገጽታ በመመለስም ማራኪ ገጽታን ለመላበስ ይረዳል።
ካካዎ፦ ካካዎን በመጠጣትም የቆዳ ላይ ጉዳትና መሸብሸበን ማስወገድ ይችላሉ።
ይህም የተጎዳን ቆዳ ለማከም፣ በቆዳ ላይ የህዋሳትን መሞት ለማስቀረት፣ ለቆዳ እርጥበታማነትና ልስላሴ ይረዳል።
የደም ፍሰትን በማስተካከልም ቆዳችን ጤናማ እንዲሆንም ይረዳል።
ከዚህ ባለፈ ግን ሲያነቡም ሆነ ንግግር አልያም ገለጻ ሲያደርጉ የሚያሳይዋቸው የፊት ገጽታዎችም የራሳቸው ተፅዕኖ እንዳላቸው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ለዚህ ደግሞ በተቻለ መጠን ሲያነቡ የንባብ መነጽር መጠቀም፤ ከፊት ገጽታ መለዋወጥ ብዛት በሂደት የቆዳ ላይ መሸብሸብ እንዳይከሰት ያደርጋል።
መነጽር ማድረግዎ ሲያነቡ አይንን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመውሰድ የማንሸዋረር ልማድን ለማስቀረትም ይረዳል።
በሃኪሞች የሚመከሩና የጎንዮሽ ጉዳት የሌላቸውን የቆዳ ላይ ቅባቶችን በመጠቀምም፥ ቆዳዎን እርጥብና ለስላሳ በማድረግ የቆዳ ላይ መሸብሸብን መከላከልም ይችላሉ።