በብሪታኒያ የኦክስፎርድ እና የበርሚንግሃም ተመራማሪዎች የቲቢ በሽታን በአጭር ጊዜ የሚለይ የዲኤንኤ የምርመራ ውጤቶችን በፍጥነት ማግኘት የሚያስችል ዘዴ ይፋ አድርገዋል።
ተመራማሪዎቹ ጄኖም ሲኩዌንሲንግ በተባለ የምርመራ ስልት የበሽታውን እያንዳንዱን ጎጂ ህዋስ ዲኤንኤ በአጭር ጊዜ መለየት ችለናል ነው ያሉት፡፡ግኝቱ የቲቢ ህሙማኑ በሽታው ታውቆ መድሃኒቱን ለመጀመር ይወስድባቸው የነበረውን ረጅም ጊዜ በጥቂት ቀናት እንዲጀምሩ የሚያስችል የምርምር ውጤት መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
ጄኖም ሲኩዌንሲንግ የምርመራ ሂደት የተለያዩ የዲኤንኤ ናሙናዎችን በመውሰድ ከሳምንት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ የምርመራ ውጤቱን እንዲያገኙ እና መድሃኒት እንዲጀምሩ የሚያስችል ነው፡፡
የቲቢን በሽታ በፍጥነት መርምሮ ውጤቱን ማግኘት ህሙማኑ ቶሎ መድሃኒት እንዲጀምሩ በማድረግ በሽታው እንዳይጠነክር እነሱም እንዲድኑ ለማድረግ ይረዳል፡፡ይህ ባይሆን ግን በምርመራ መራዘም ምክንያት በሽታው በህሙማኑ ውስጥ እየጠነከረ ሄዶ ለከፋ ጉዳት ይዳርጋቸዋል፡፡
የብሪታኒያ የጤና ሚኒስትሩ ጀረሚ ሁንት ግኝቱን የበርካቶችን ህይወት ለመታደግ የሚረዳ ብለውታል፡፡ማይክሮ ባዮሎጂስቱ ፕሮፌሰር ግሬስ ስሚዝ እንዳሉት፥ በሽታውን ቶሎ በመለየት ቲቢ ከሆነ የፀረ- ቲቢ መድሃኒት በፍጥነት እንዲጀምሩ ያስቻለ ግኝት ነው፡፡
የብሪታኒያ ህብረተሰብ ጤና ተቋም ይህ ዓይነቱ የቲቢ በሽታ ምርመራን በአጭር ጊዜ ይፋ ማድረግ የሚያስችል ሙከራ በዓለም የመጀመሪያው ነው ብሏል፡፡
የቲቢ በሽታ ስርጭት በብሪታኒያ አሁን እየቀነሰ ቢሆንም በአውሮፓ ከፍተኛ የበሸታው ተጠቂዎች የሚገኑት በዚህች ሀገር ነው፡፡
ቲቢ በዓለማችን በየቀኑ የ5 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ በሽታ መሆኑን የኣለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
የዓለም የቲቢ በሽታ ቀን በየዓመቱ በፈረንጆች መጋቢት 24 ይከበራል፤ ዘንድሮ “ቲቢን በጋራ እንግታ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው፡፡
የዘንድሮው ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር በፈረንጆች 1882 ጀርመናዊው ዶክተር ሮበርት ኮች የማይኮ ባክቴሪየም ቲዩበርክሊስስ ወይም የቲቢ በሽታ አምጭ ባክቴሪያን ያገኙበትን ዕለት በማስታወስ ይሆናል፡፡ምንጭ፦ ቢቢሲ