በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በደቡብ ሱዳን ጁባ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5 ሺ በላይ አትሌቶች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚያካሂድ ተገለፀ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አይሸሹም ተካ ከተባሉ ግለሰብ ጋር በመተባበር የሚያካሂዱትን የሩጫ ውድድር አስመልክቶ ትናንት መግለጫ በተሰጠበት ወቅት፣የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራችና የቦርድ ሊቀመንበር አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እንደገለፀው፣ ስፖርት የሰላም ተምሳሌት ነው። ስፖርት ፆታ ዘር ቀለም ሃይማኖት አይለይም። ስፖርት ሁለት አገራትን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ያስተሳስራል። አንድነትን ያጠነክራል።
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የደቡብ ሱዳን ታላቁ ሩጫም በአገሪቱ ዜጎች መካከል ሰላምና አንድነትን ለማጎልበትና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ የዓለምን ትኩረት እንዲያገኝ ዓላማው ያደረገ ነው።
«የጎረቤት አገራት ሰላም ለኢትዮጵያ ሰላም መሆን ፋይዳው የጎላ ነው፣ የደቡብ ሱዳን ችግር የዓለም ህዝብ ችግር ነው፤ እኔም የዓለም ህዝብ አካል እንደ መሆኔ የደቡብ ሱዳናውያን ችግር ይመለከተኛል» ያለው አትሌት ኃይሌ፣ ለአገሪቱ ሰላም መሆን የድርሻውን ለመወጣት የለ ምንም ክፍያ ዓላማውን ለመርዳት መወሰኑን በውድድሩ ላይ የሰላምን ዋጋ የሚመለከት መልዕክት እንደሚያስተላልፍ አስረድቷል።
ታላቁ ሩጫ ከአገር ውስጥ ውድድሮች በተጓዳኝ የተለያዩ መሰል ውድድሮችን የማዘጋጀት ልምድ እንዳለው በመጥቀስ ፣በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚካሄደው ውድድር ስኬታማ በሆነና የታለመለትን ዓላማ ባሳካ መልኩ እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳዳር ጄምስ ሞርጋን በበኩላቸው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መሆን በርካታ ጥረቶችን ስታካሂድ ቆይታለች፣ አሁንም ይህን ተግባሯን አጠናክራ ለች፡፡
«ስፖርት ለሰላምና ለአንድነት ትስስር ያለውን ፋይዳ መጠቀም በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ያለውን የሰላም እጦትና የድርቅ ክስተት ገፅታ ለመቀየር ፍላጎት አለን፣ የጦርነት ምዕራፍ ዳግም ላለመክፈት መዘጋትና ስለ ጦርነት ማውራት ማቆም እንፈልጋልን፣ አሁን ስለ ሰላምና ኢንቨስትመንት ነው ማውራት የምንፈልገው» ያሉት አምባሳደሩ፣ ውድድሩም ኢትዮጵያ ሁሌም ከደቡብ ሱዳን ጎን እንደሆነች ምስክር የሚሰጥና የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን አስታውቀዋል።አሁን ላይ በአገሪቱ አንፃራዊ የሚባል ሰላም መስፈኑንና ውድድሩን የሚያስተጓጉል የፀጥታ ችግር አለመኖሩን አስገንዝበዋል።
በደቡብ ሱዳን ኑሮአቸውን ያደረጉትና በአገሪቱ በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩት አቶ አይሸሹም ተካ በበኩላቸው፣አሁን ላይ በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ሌላኛው በአገሪቱ ህልውና ላይ የተጋረጠ ስጋት መሆኑን ተናግረ ዋል፡፡
በአገሪቱ የሚካሄደው ውድድርም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጥና ለችግሩ መፍትሄ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
«ኑሮዬና ሥራዬ በደቡብ ሱዳን እንደመሆኑ ውድድሩን ለማካሄድ በአገሪቱ አሁን ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታን በሚመለከት እኔ ምስክር መሆን እችላለሁ» ያሉት አቶ አይሸሹም፤አሁን ላይ በአገሪቱ አንፃራዊ የሚባል ሰላም መስፈኑንና ውድድሩን የሚያስተጓጉል የፀጥታ ችግር አለመኖሩን አስታውቀዋል ።
«ትናንትን መቀየር ባንችል ነገን መቀየር እንችላል» ያሉት አቶ አይሸሹም፣ውድድሩን ለማዘጋጀት ያሰቡትም ነገን የተሻለ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆችም ይህን ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር በትብብር ለመስራት መፍቀዳቸው ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጡ የሚመሰክር መሆኑን አብራርተዋል።
እ.ኤ.አ በ2011 ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ከ2013 ጀምሮ በመንግሥትና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በተነሳ የስልጣን ሽኩቻ ስትታመስ ለቆየችው ደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚካሄደው ይህ የመጀመሪያው የደቡብ ሱዳን ታላቁ ሩጫ 10 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከ 5 ሺ በላይ ተወዳዳሪዎችም ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። ውድድሩም ከ17 ቀናት በኋላ በአገሪቱ ዋና መዲና ጁባ የሚካሄድ ይሆናል።
– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/sport/item/11829-2017-03-21-18-00-48#sthash.t0OBQ6qu.dpuf