የአለማችን እድሜ ጠገብ አዛውንት በ117 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ተሰማ።
ጣሊያናዊቷ ኤማ ሞሬኖ በሰሜናዊቷ ቨርባኒያ ከተማ በሚገኘው መኖሪያቸው ነው ያረፉት።
ወይዘሮ ኤማ ሞሬኖ በፈረንጆቹ ህዳር 18 99 ተወልደው ረጅም እድሜ የኖሩ አዛውንቷ እመቤት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
እድሜ ጠገቧ ወይዘሮ በኖሩባቸው ጊዜያት ሁለቱም የአለም ጦርነቶች ሲካሄዱ አይተዋል።
ሃገራቸው ጣሊያንንም ከ90 በላይ መንግስታት ሲመሯት ተመልክተዋል።
ረጅም እድሜን ለመኖር የታደለ ቤተሰብ አባል መሆናቸውን ረጅም እድሜ ለመኖራቸው ምክንያት አድርገው ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈም ለበርካታ አመታት በቀን ሶስት እንቁላል መመገባቸው የምድራችን ረጅም እድሜ ኗሪ ለመሆን እንዳበቃቸውም ተናግረዋል።
እርሳቸው ከ90 አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በቀን ሶስት እንቁላል እየተመገቡ ያሳለፉ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ሁለቱን በጥሬው እንደሚመገቧቸው ገልጸዋል።
እድሜያቸው 75 አመት እስከሚሆንም በስራ ላይ ነበሩ።
በእነዚህ ጊዜያት ታዲያ አንድ ጊዜ ብቻ ትዳር መስርተው ስለማቋረጣቸውም ይናገራሉ።
በ26 አመታቸው የመሰረቱት ትዳር ምቹ እና አስደሳች ባለመሆኑም ትዳራቸውን ማቋረጣቸውን ነው የተናገሩት።
በአንድ ወቅትም ነጻነታቸውን የሚጋፋ ነገር እንደማይወዱ ነው የገለጹት፤ ማንም እንዲቆጣጠራቸው እንደማይፈልጉም ይጠቅሳሉ።
በ19 38 በትዳር ያፈሩት የስድስት ወር ጨቅላ ከሞተ ከአመት በኋላም ትዳራቸውን ፈተው በብቸኝነት ኖረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከሞተ ወጣት ጋር ፍቅር ቢይዛቸውም ከዚያ በኋላ ግን ትዳር ለምኔ ብለው አሳልፈዋል።
ሁለት ግዙፍ የአለማችን የጦርነት ክስተቶችን ክፍለ ዘመን በተሻገረው እድሜያቸው ያጣጣሙት እድሜ ጠገቧ እመቤት እና የአለማችን ረጅም እድሜ ኗሪ በመጨረሻም በ117 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ