የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ከፖለቲካና ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? የህግ ባለሙያዎች የአዋጁ መራዘም ከህገ መንግስት ውጪ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ፖለቲከኞች በበኩላቸው፤ህዝቡ ህገ መንግስታዊ መብቱን ተነፍጎ ወታደራዊ አገዛዝ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ወድቋል ይላሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ፖለቲከኞችንና የህግ ባለሙያዎችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
‹‹አስቸኳይ ሁኔታ በሌለበት አስቸኳይ አዋጅ አይታወጅም››
አቶ ተማም አባቡልጉ (የህግ ባለሙያ)
በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲባል መጀመሪያ አስቸኳይ ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ይሄ ሲኖር ነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው። አስቸኳይ ሁኔታ በሌለበት አስቸኳይ አዋጅ አይታወጅም፡፡ በኢትዮጵያ ወቅታዊ እውነታ አስቸኳይ ሁኔታ በሌለበት ቦታ ሁሉ አዋጁ መታወጁ፣ አስቸኳይ አዋጅ አስፈላጊ እንዳልነበረ ያሳያል፡፡ አዋጁ የፖለቲካ ፍላጎትን ማሳኪያ ነው የሆነው፡፡ በመሠረቱ ግን አዋጁ አስቸኳይ ሁኔታን ለማስወገድ የሚወጣ አስፈላጊነት ያለው አዋጅ ነው። ግልጽ ከሆነ አደጋ ራስን ለመከላከል የሚጣል አዋጅ ነው፡፡ በሃገራችን ግን አስቸኳይ ነገር በሌለበትም ባለበትም ቦታ በእኩል መታወጁ ከህግ ውጪ ነው፡፡ ህገ ወጥ ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝብን መብት በግልፅ የሚገድብ እንደመሆኑ ተጥሎ መቆየትም የለበትም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አስቸኳይ ሁኔታ አይነጣጠሉም፡፡
አሁን አስቸኳይ ሁኔታ አለ ወይ ነው ጥያቄው? በመደበኛው የህግ ስርአት ማስተናገድ የማይቻል ችግር አለን? ይሄ መታየት አለበት፡፡ እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ የሚጣል አዋጅ ግን በህግ ሽፋን ራስን እንደ መከላከል ነው፡፡ መሬት ላይ የሚታይ አስቸኳይ ሁኔታ በሌለበት የሚጣል አዋጅ ደግሞ ፀረ-ህገ መንግስት ነው፡፡ ፀረ ህግ ከሆነ ደግሞ ፀረ-ሠላም ነው የሚሆነው፡፡ የህግ የበላይነት ሳይኖር አስተማማኝ ሠላም አይኖርም፡፡
ምንም በሌለበት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው፡፡ ሃገሪቱ የፈረመቻቸውን አለማቀፍ የሠብዓዊ መብት ስምምነቶች የሚጥስ በመሆኑም ከህግ ውጪ ነው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በአማራ ክልል ሆኖ በኦሮሚያም ማወጅ፣ ችግሩ ያለው በኦሮሚያ ሆኖ በደቡብ ማወጅ ከህገ መንግስቱ ውጪ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የሚለው ችግር ሲኖር፣ የአስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር ይታወጃል ነው፡፡ አስቸኳይ ሁኔታ በተፈጠረበት ቦታ ነው አስቸኳይ አዋጅ ተለይቶ የሚታወጀው፡፡ አዲስ አበባ ምንም ባልተፈጠረበት ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ህገ ወጥነት ነው፡፡
ይሄን በምሣሌ ለማስረዳት ለምሳሌ የጎርፍ አደጋ በኦሞ ወንዝ ላይ ቢያጋጥም፣ በአባይ ወንዝ ላይ ለምንድን ነው የሚታወጀው? አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ይሄንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ህዝቡ ያለ አግባብ መብቱ ስለሚታገድበት ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡
አዋጅ መራዘሙም ኮማንድ ፖስት ወይም ወታደራዊ እዙን ህጋዊ እንደ ማድረግ ነው፡፡ አሁን ያለው በአጠቃላይ ወታደራዊ አገዛዝ ማለት ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በህገ መንግስቱ ላይ የሌለ ወታደራዊ ሃይል ማለት ነው፡፡ ይህ ወታደራዊ ሃይልና የሲቪል አስተዳደሩ ቅንብር ፈጥረው፣ ህዝቡን መብት የማሳጣት ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲያስቀጥሉ፣ አስቸኳይ ድንገተኛ እርምጃ መውሰድ ቀርቷል ብለዋል፡፡ ይሄ ከቀረ ደግሞ ኮማንድ ፖስቱ መፍረስ አለበት፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም መነሣት አለበት፡፡
በፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰው ማሠር ከተቻለ፣ አስቸኳይ ሁኔታ የለም ማለት ነው፡፡ ይሄን ማሻሻላቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህ አንፃር ከተመለከትነው ኮማንድ ፖስቱም አዋጁም አያስፈልጉም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ልክ ከህገ መንግስቱ ውጪ እንደተቋቋመው ፀረ ሽብር ግብረ ሃይል፣ ኮማንድ ፖስቱንም ቋሚና ህጋዊ ለማድረግ የተፈለገ ነው የሚመስለው፡፡ እነዚህ ወታደራዊ እዞችን ቋሚ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አግባብ አይደለም፡፡ ወታደራዊ መንግስት መፍቀድ እንደ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው እያንዳንዱ እየተካሄደ ያለው፣ ከህገ መንግስቱ ውጪ ነው የምለው፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተወሰኑ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ተገልጿል፡፡ ግን የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባና ሠልፍ ማድረግ ያለ ኮማንድ ፖስቱ ፍቃድ የተከለከለ ነው፡፡ ይሄ ክልከላ እስካሁን አልተነሣም። ከዚህ በፊት በአዋጅ ቁጥር 7/83 ሠላማዊ ሠልፍ ማሣወቅ ብቻ ይበቃል የሚል አለ፡፡ ይሄ ህግ የሚያስፈልገው የመንግስት አካል ማሳወቅ በቂ ነው በሚለው ህግ ተጠቅሞ፣ ለሠላማዊ ሠልፍ እውቅና እንዳይሰጥና ኮማንድ ፖስቱ እየፈቀደ ብቻ እንዲቀር ስለተፈለገ ይመስላል፡፡ ወይም ደግሞ እየተለመደ ሄዶ፣ ኮማንድ ፖስቱ ይሄን ለመፍቀድ ብቻ የተቋቋመ መደበኛ ተቋም እንዲሆን ተፈልጎም ሊሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ የፈረመችው የ1948 አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ አንቀፅ 8፣ 18፣ 19 እና 20 የሚባሉት ላይ የመሠብሠብ መብትን መከልከል ወንጀል ነው ይላል፡፡ የአፍሪካ ኮንቬንሽንም ይሄንኑ ይላል፡፡ እነዚህን ነገሮች በቋሚነት ለማገድ የተፈለገ ነው የሚመስለው፡፡
ኮማንድ ፖስቱን በዚህ መንገድ ቋሚ አድርጎ ለማስቀጠል የተፈለገ ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ማንኛውንም የወንጀል ጉዳይ የማጣራት ስራ የፖሊስ መሆኑ በህግ ተደንግጎ እያለ፣ የፀረ-ሽብር ግብረ ሃይል በሚል ተቋቁሞ፣ ዛሬም ድረስ ተለምዶ መቅረቱ ነው፡፡
————-
“መፍትሔው መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጦች ማድረግ ነው”
አቶ ገብሩ አስራት (ፖለቲከኛ)
አዋጁ መጀመሪያ ሲታወጅ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወጣቱና ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ለአመፅ ተነሳስቶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ህዝቡ ያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎች፣ የውክልና፣ የአስተዳደር፣ የሙስና፣ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡ በተደራጀ መልኩ ባይሆንም በሁሉም አካባቢዎች የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አመፁም የነዚህ ጥያቄዎች ውጤት እንጂ በራሱ ክስተት አልነበረም፡፡ አመፁን ለማስታገስ ሲባል ይሄ አዋጅ ታወጀ፡፡ አዋጁ ሲታወጅ መሰረታዊ የሚባሉ ጥያቄና ችግሮችን ለመፍታት ሙከራ አልተደረገም። ህዝብ የጠየቃቸው ጥያቄዎች፣ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና ብዙኃን ማህበራት የሚያነሷቸውና የሚያንፀባርቋቸው ችግሮች በሙሉ እየተመለሱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ያለው አማራጭ ሁለት ብቻ ነበር፡፡ አንደኛው አዋጁን አስቀጥሎ ሀገሪቱን መግዛት፣ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ለውጦች ማድረግ ነው፡፡ ኢህአዴግ የመረጠው መሰረታዊ የፖለቲካ መፍትሄዎችን መስጠት አይደለም፤ ህገ መንግስቱ ይፈቅድልኛል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም ነው፡፡
ህዝቡ ያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ስላልተመለሱ በማንኛውም ሰዓት ችግር ይነሳል የሚል ስጋት አለው፤ ኢህአዴግ፡፡ ስለሆነም አዋጁን አራዝሞታል፡፡ ግን እንደተባለው ለ6 ወራት ሊቆይና በወራትም አዋጁ ሊነሳ ይችላል የሚል ግምት ነው የነበረው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ለመሰረታዊው ችግር መፍትሄ ይሰጣል የሚል ግምት ነበረ፡፡ ይሄን አላደረገም፡፡ ይሄን ካላደረገ ደግሞ ስጋት አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለሚፈጠረው ክፍተት ማስታገሻ ሆኖ ያገኘው አዋጁን ማራዘም ብቻ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነው እየሄደ ያለው የሚመስለኝ፡፡
በዚህ ሀገር ዋናው ችግር ህዝብ ማለት ኢህአዴግ ማለት እንደሆነ ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡ ኢህአዴግ አንድ ነገር ካለ፣ ህዝብ ያለው ተብሎ ነው የሚነገረው እንጂ ኢህአዴግ በትክክል ህዝብን አናግሮም አያውቅም፡፡ የራሱን ድምፅ ለማዳመጥ ካልሆነ በስተቀር ነፃ የሆነ ድምፅ ሰምቶ አያውቅም፡፡ ይሄ አዋጅ ሲታወጅም ህዝቡን አላማከሩም፡፡ እንዲያውም የአዋጁ መንደርደሪያ እንደማስታውሰው፣ በነበረው ሁኔታ ማስተዳደር ስለማይቻል ይህን አዋጅ አውጀናል ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ ህዝቡን ሳያማክሩ ያወረዱትን አዋጅ፣ ህዝቡን አማክረን እንዲቀጥል ፈልጓል ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡
የትኛውስ ነፃ ተቋም አለና ነው፣ ይሄ ጥናት ተደረገ የሚሉት? ያሉት የመንግስት ተቋማት ከመንግሥት ተፅዕኖና ቁጥጥር ነፃ አይደሉም፡፡ ይሄ ውሃ የማይቋጥር፣ የማይመስል ነገር ነው፡፡ በየትኛውም ሃገር ህዝብ ነፃነት ይፈልጋል እንጂ ወታደራዊ በመሠለ አገዛዝ ልገዛ የሚል ህዝብ ይኖራል ማለት አያስኬድም፡፡
ይሄ ህዝቡን መናቅ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ የተወሰኑ የፓርቲ አባላት ይሄን አዋጅ ሊፈልጉት ይችላሉ፤ ነገር ግን ህዝቡ ደግፏል ማለት ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡
መንግስት ያለው ምርጫ ለህዝብ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ወይም ደግሞ በጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጅ መግዛት ብቻ ነው፡፡ አዋጁ ከ4 ወር በኋላ ቢቋረጥ እንኳ ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ መልሶ ማገርሸቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የችግሩን ምንጭ መነሻ አድርጎ መፍትሄ እስካልተበጀለት ድረስ ውጤ “የአዋጁ መራዘም ህገ መንግስቱን ይፃረራል”
አቶ አዲሱ ጌታነህ (የህግ ባለሙያና ፖለቲከኛ)
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማለት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት፣ የዲሞክራሲና የሥነ ሥርአት መብቶችን ለጊዜው ተፈፃሚነታቸውን ማስቆምና ለተፈጠረው ነገር መንግስት በራሱ መርህ የሀገሪቱን ህጎች አስቀርቶ፣ አመቺ በሚመስለው መንገድ ሀገሪቱን ለማስተዳደር መምረጥ ማለት ነው፡፡ ሀገሪቱ የምትተዳደረው መንግስት ለራሱ በመረጠው አመቺ ሁኔታ ይሆናል፡፡ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ይቀራሉ ማለት ነው፡፡
ህዝቡ እነዚህ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ቀርተው መንግስት በፈለገው መንገድ እንዲያስተዳድረው መረጠ ማለት በእውነት ከብዙ ነገሮች ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መንግስት እንዲህ ያሉ አሃዞችን ያወጣል፡፡ ግን ለየትኛው የህብረተሰብ ክፍል መጠይቆች ተበትነው ነው? የትኛው አካባቢ ላይ ነው ጥናቱ የተደረገው? በየትኛው ስልት ተጠንቶ ነው ይሄ ቁጥር የመጣው? ግልፅ አይደለም፡፡ በኢህአዴግ ታሪክ እንዲህ ያለ ግልፅና የጠራ መረጃ ኖሮንም አያውቅም፡፡ 82 በመቶ የተባለውም የት ቦታ? እነማን ተጠይቀው? በምን ዓይነት ዘዴ ተጠና? ማን አጠናው? በየትኛው ወቅት ተጠና? የሚሉት ነገሮች ግልፅ አይደሉም። ይሄ ባልሆነበት ዝም ብሎ 82 በመቶ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን 82 በመቶ ህዝብ ይደግፈዋል ማለት አብዛኛው ህዝብ የሲቪል አስተዳደር አልፈልግም፤ የምፈልገው ወታደራዊ መንግስት ነው አለ እንደ ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በዚህ ዘመን ይኖራል ተብሎ የማይታሰብ አስተሳሰብ ነው፡፡ እንደውም ተቃውሞዎቹን ስናይ ወታደራዊ አገዛዝ ይብቃ! አምባገነናዊ አገዛዝ ይብቃ! የሚሉ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ስለዚህ ይሄ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 93፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለሚደነገግበት ሁኔታ ምን ይላል የሚለውን ስንመለከት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም፣ የውጭ ወረራ ሲመጣና በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት፣የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ የማይቻል ሲሆን ነው የሚለው፡፡ አሁን መንግስት ይሄን አዋጅ ለማራዘም ዋነኛ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው፣ በክልሎች ድንበር አካባቢ አሁንም ግጭቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ይሄ ማለት በመደበኛ የህግ ስርአት የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ አልተቻለም ማለት ነው? ወረቀት መበተንን በመደበኛ የህግ ስርአት ማስከበር አልተቻለም ማለት ነው? እኔ አይመስለኝም፡፡ አዋጁ ለመራዘሙ በቂ ምክንያት የለውም፡፡
የክልሎችን ሉአላዊነት ትተን እንኳ ጉዳዩን ብንመለከተው፣ የአዋጁ መራዘም የህገ መንግስቱን አንቀፅ 93 መፈፀም አያሟላም፡፡ ወረቀት መበተን፣ አንዳንድ ያልተያዙ ሰዎችን መያዝና የድንበር ግጭቶችን ማስቆም ከመደበኛ የህግ ስርአት በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ በዚህ መንገድ አንቀፅ 93 የማያሟላ ከሆነ ደግሞ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 9 ጋር ስንሄድ፣ ማንኛውም የመንግስት ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ የሚፃረር ከሆነ ውድቅ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ ይሄ አዋጅ ህገ መንግስቱንም የጣሰ በመሆኑ፣ አጠቃላይ የሀገሪቱን ደህንነትና ሰላም የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡ ይሄን ስል የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39፣ የክልሎች ሉአላዊነትን የሚደነግገው አንቀፅ ተጥሶ፣ በመላ ሀገሪቱ መታወጁ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡
የአዋጁ መራዘም ህገ መንግስቱን የሚጥስ ከመሆኑም ባሻገር የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታም የሚጎዳ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን የቱሪዝም ዘርፉን በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ የውጪ ኢንቨስትመንትንም ይጎዳል። የኔ ስጋት በዚሁ ከቀጠለ ሀገሪቱን ለኢኮኖሚ ድቀትም ይዳርጋል የሚል ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኢኮኖሚ ጉዳት ከማስከተሉም ባሻገር ህዝብን በመንግስት ላይ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ህዝብ ደግሞ ውሳኔው ምን እንደሚሆን አይታወቅምና፣ እኔ መንግስትን የማሳስበው ጉዳዩን ደጋግሞ እንዲያጤነው ነው፡፡
“የአዋጁ መራዘም ያልበረደ ትኩሣት እንዳለ ያሳያል”
አቶ ግርማ ሰይፉ (ፖለቲከኛ)
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተራዘመበት ሁኔታ የፖለቲካ እውቀትን የሚፈታተን ነው፡፡ እኔ ሳስብ የነበረው እንደ ማንኛውም ጊዜ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ወስደው ይተዉታል የሚል ነበር፡፡ ወትሮም ቢሆን የፍ/ቤት ትዕዛዝ የሚባለው ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት በመሆኑ አሁን ካለው ብዙም አይለይም፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ ከመብት አኳያ ብዙም ለውጥ ባይኖረውም በሀገሪቱ ላይ ግን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል። ቱሪዝሙ ይጎዳል፡፡ የአዋጁ መራዘም እኛ የማናውቀው ያልበረደ ትኩሳት እንዳለም ያሳየናል፡፡ ስለዚህ ይሄን ትኩሳት ዝም ብለው ቢለቁት የስልጣን እድሜያቸውን እንዳያሳጥርባቸው ሰግተዋል ማለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 82 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ደግፎታል ያሉት፣ ለመራዘሙ ምንም አሳማኝ ምክንያት አይደለም፡፡ ምክንያታቸው ያልበረደው ትኩሳት ነው፡፡ እንዲያውም 82 በመቶ የሚሉት የራሳቸውን አባላት ጠይቀው መሆን አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ የሚያሳየው ከራሳቸው አባላት መካከልም 18 በመቶዎቹ አዋጁን እንደማይደግፉት ነው፡፡
ህዝቡ መቼም መብቴን ገድቡልኝ፣ የማየውን ቴሌቪዥን ምረጡልኝ ይላል የሚል ግምት የለኝም። ይሄ ማለት ከባርነትና ከነፃነት የቱን ትመርጣለህ እንደ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ውስጥ ሰው እንዴት ባርነትን ይመርጣል? ምናልባት ምርጫውን ከሰላም እና ከብጥብጥ የቱ ይሻላል ብለውት ሊሆን ይችላል። መቼም ከሰላምና ከብጥብጥ አማራጭ ቢቀርብልን ሁላችንም ሰላምን ነው የምንመርጠው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው የቀረበበት መንገድ በሚገባ መታየት አለበት። ወይም ደግሞ የተጠየቁት ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም ማለት ነው፡፡
በፐርሰንት የተሰሉ መረጃዎች ሲነገሩ የጥናቱ አሰራር ዘዴ መገለጽ አለበት፡፡ ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ዝም ብሎ 82 በመቶ ማለት በጣም ከባድ ነገር ነው። አንድ በስታትስቲክስ ትምህርት ውስጥ የሚነገር ነገር አለ፡፡ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች ይደፈራሉ የሚል መረጃ ይወጣል። እንዴት እንዲህ ይሆናል በሚል አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲጣራ፣ እዚያ ያሉት ሴቶች ሁለት ናቸው። ከሁለቱ አንዷ ነች የተደፈረችው፡፡ ይሄ ተይዞ ነው 50 በመቶ የተባለው፡፡ ይሄም እንደዚህ ይመስለኛል። አራት ሰዎችን ጠይቀው ያሰሉት ፐርሰንት ሳይሆን አይቀርም፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቼም ቢሆን የፖለቲካ ችግር መፍትሄ አይሆንም፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ የሚሉትም ቀልድ ይመስለኛል፡፡ ድሮ ከሚያነጋግሩት የህብረተሰብ ክፍል የተለየ ሌላ የህብረተሰብ ክፍል ቢያነጋግሩ ነበር የተለየ ውጤት የሚመጣው፡፡ በአመራር ደረጃም ቢሆን እርስ በእርሳቸው ተሰባስበው የሚያመጡት ነገር አይኖርም፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ሰበሰቡ ግን አልሰሟቸውም፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን ለመምህራኑ ነግረዋቸው ነው የወጡት፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ለውጥ የሚመጣው? ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርም ድርድር ብለው ጀምረዋል ግን አሁንም እነሱ በሚሉት መንገድ ብቻ እንዲመራ ስለፈለጉ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ተብሏል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ለውጥ ለማምጣት ሌላ መፍትሄ መፈለግ አለ “የተራዘመው አዋጅ በድጋሚ ሊጤን ይገባዋል”
አቶ አዳነ ጥላሁን (ፖለቲከኛ)
እኔ ጠብቄ የነበረው የአዋጁን መነሳት እንጂ ለ4 ወራት ድጋሚ መራዘምን አልነበረም፡፡ መንግስትም የሚያነሳው ነበር የሚመስለው፡፡ አንደኛ ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ ሀገር አረጋግቶልኛል፤አስተማማኝ ሰላም ላይ ደርሻለሁ ሲል ነበር የተናገረው፡፡ በሌላ በኩል ከታች እስከ ላይ ያለው አመራር በጥልቅ ተሃድሶ እያለፈ ስለሆነ ችግሮችን እያየሁ መፍትሄ እያስቀመጥኩ ነው ተብለን ነበር፡፡ ይሄ ከተባለ ለምን ለተጨማሪ 4 ወራት ማራዘም አስፈለገ? ይሄ የሚያሳየው ጉዳዩ ግራ አጋቢ መሆኑን ነው፡፡ ሌላው የአዋጁ መራዘም በህዝብ ፍላጎት እንደተፈፀመ ነው የተነገረን፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በየትም ሀገር ከጥንት ጀምሮ እስካሁን መንግስትን “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቴን በሙሉም ሆነ በከፊል ገድብልኝ” ብሎ ህዝብ ስለመናገሩ በታሪክም አልተዘገበም፡፡ ይሄ በኛ ሃገር ተጠይቆ ከሆነ፣ ይሄን በማለቱ በአለም ታሪክ የኛ ህዝብ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የአዋጁ መራዘም ህዝብን በፍርሃት ቀለበት ውስጥ አስገብቶ፣ ስልጣንን ለማራዘም የሚደረግ ጥረት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ የህዝብ ቅሬታ ባልተፈታበት ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመጣ አስተማማኝ ሠላም አይኖርም፡፡ በአዋጅ የህዝብን መብት ማፈን ዝምታን ነው የሚያመጣው፡፡ ዝምታ ደግሞ በራሱ አመፅ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ የተራዘመው አዋጅ ጉዳይ በድጋሚ ሊጤን ይገባዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ባለፈው ሳምንት እትማችሁ፣ በሠብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት ጉዳይ ባቀረባችሁት አጀንዳ ላይ አንድ የመንግስት ባለስልጣን በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ሀገር በቀል ዲሞክራሲ አላት ማለታቸው አስገርሞኛል፡፡ ዲሞክራሲ ማለት የህዝብ አገዛዝ ማለት ነው፡፡ እኔ ከጥንት አንስቶ እስካሁን በኢትዮጵያ የህዝብ አገዛዝ ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ ያውም በራሳችን ልምድ፣ ባህልና ትውፊት የተቃኘ ማለት ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ዲሞክራሲ ከውጭ የመጣ እንጂ ሀገር በቀል አይደለም፡፡ ይሄ አመለካከት መስተካከል አለበት፡፡ ዲሞክራሲ ቢኖር ኖሮ፣ እስከ ዛሬ የህዝብ የመብት ጥያቄ መልስ ባገኘ ነበር፡፡