የምንወስደው ምግብ በፀጉራችን እድገት ላይ ቀጥተኛ የሆነ አዎንታዊ ወይንም አሉታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ለጤናማ የፀጉር እድገት በቫይታሚን (ኤ፣ ሲ፣ ኢ፣ ቢ5፣ ቢ6፣ እና ቢ12) እንዲሁም በዚንክ፣ ፕሮቲን፣ ሰልፈር እና ሲሊካ የበለፀጉ ምግቦችን መውሰድ እንደሚገባ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።
የፀጉር መርገፍ እና መሳሳት ችግርን ለመቅረፍ ለፀጉር እንክብካቤ የሚውሉ ምርቶችን ለመግዛት ብዙ ገንዘብ ከማውጣት አመጋገባችንን ማስተካከሉ አዋጪ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት 10 የምግብ አይነቶችም የፀጉር እድገትን በማፋጠን የፀጉር መሳሳት ችግርን ያቃልላሉ ተብሏል።
1. እንቁላል
ፕሮቲን ለፀጉር እድገት ቀዳሚው አጋዥ ንጥረ ነገር ነው። በመሆኑም እንደ እንቁላል ያሉ በፕሮቲን የበለፀጉ ምግቦችን መውሰድ የፀጉርን ጤንነት ለመጠበቅ ይረዳል።
እንቁላል ከፕሮቲን በተጨማሪ የቢዮቲን እና የቢ ቫይታሚኖችን የያዘ በመሆኑ የፀጉር መሳሳት ችግርን ለመከላከል ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።
2. አሳ
አሳ ለአዕምሮ፣ ለደም ቧንቧዎች፣ ለቆዳ እና ለፀጉር ጤና ወሳኝ ሚና አለው።
አሳዎች በኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ የበለፀጉ በመሆናቸውም የፀጉር እድገት እንዲፋጠኑ ይረዳሉ።
የፕሮቲን፣ ሚኒራል እና ቫይታሚን ቢ ይዘት ያላቸው አሳዎችን መመገብ የፀጉር ድርቀትን እና መሳሳትን ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል።
3. የከብት ስጋ
የከብት ስጋ የፕሮቲን፣ ቫይታሚን ቢ፣ ብረት እና ዚንክ የበለፀገ በመሆኑ ለጤናማ የፀጉር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።
በሰውነታቸው ውስጥ ከፍተኛ ኮሊስትሮል ያላቸው ሰዎች የከብት ስጋን ከመመገብ ይልቅ ሌላ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው ምግቦችን ቢወስዱ ይመከራል።
4. ጥራጥሬዎች
አነስተኛ ካሎሪ በያዘ ፕሮቲን፣ ፋይበር፣ ቫይታሚን ቢ፣ ቫይታሚን ሲ፣ ዚንክ እና ሚኒራሎች የበለፀጉ ጥራጥሬዎችም ለፀጉር እድገት አስተዋፅኦቸው የጎላ ነው ተብሏል።
ቦለቄ፣ ምስር፣ ሰሊጥ፣ አተር እና መሰል ጥራጥሬዎች የፀጉር መሳሳት ችግርን ለመከላከል ይረዳሉ።
5. የሱፍ ፍሬ
የሱፍ ፍሬ የፀጉር መሳሳትን የሚከላከሉ እንደ ፕሮቲን፣ ዚንክ፣ ሴለኒየም፣ ባዮቲን፣ ፖታሲየም፣ መዳብ፣ ብረት፣ ቫይታሚን ኢ እና ቢ፣ ማግኒዥየም እና ካልሲየም የመሳሰሉ በርካታ ንጥረ ነገሮችን ይዟል።
በተለምዶ የፈረንጅ ሱፍ የምንለው ተክል ፍሬ በኦሜጋ 5 ፋቲ አሲሰዶችም የበለፀገ መሆኑ ይነገራል።
6. ለውዝ
በቫይታሚን፣ ሚኒራልስ፣ ጤናማ ስብ፣ በፕሮቲን እና የፀጉር መሳሳት ችግርን ለመከላከል የሚረዱ ፎቶኬሚካልስ በለውዝ ውስጥ በስፋት እናገኛለን።
7. ስፒናች
በቫይታሚን ቢ፣ ሲ እና ኢ፣ በፖታሲየም፣ ካልሲየም፣ ብረት፣ ማግኒዥየም እመና ኦሜጋ 3 የበለፀገው አረንጓዴው አትክልት ሲፒናች ለፀጉር እድገት ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ስፒናችን በምግብ አልያም በጭማቂ መልክ መውስድ የፀጉር እድገትን ለማፋጠን ይረዳል የተባለ ሲሆን፥ እንደ ጎመን እና ሰላጣ ያሉ አረንጓዴ አትክልቶችንም ከስፒናች በተጨማሪ መመገብ መልካም መሆኑ ተጠቁሟል።
8. አጃ
አጃ የፀጉር መሳሳትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው የሚነገርላቸውን ቫይታሚን ቢ፣ ዚንክ፣ ፕሮቲን እና መዳብ ይዟል።
ለፀጉር እድገት ይበጃሉ በተባሉት ማግኒዥየም፣ ፎስፎረስ፣ ፖታሲየም እና ብረት ያሉ ሚኒራሎችም የበለፀገ ነው።
9. ካሮት
ካሮት የፀጉር እድገትን የሚያፋጥነው ቤታ ካሮቴን ይዘቱ ከፍተኛ ነው።
የቫይታሚን ኤ ይዘቱም ጤናማ የጭንቅላት ቆዳ እንዲኖረን ይረዳል።
10. ስኳር ድንች
የፀጉር መሳሳት ችግርን የስኳር ድንችን በቋሚነት በመመገብ ልንከላከለው እንችላለን።
ስኳር ድንች ሰውነታችን ወደ ቫይታሚን ኤ የሚቀይረውና ለፀጉር እድገት ወሳኝ የሆነው ቤታ ካሮቲንን ይዟል።
የቫይታሚን ሲ፣ መዳብ፣ ብረት እና ፕሮቲን ይዘቱም ለፀጉር እድገት ከተዘረዘሩት ምግቦች ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።
ምንጭ፦ www.top10homeremedies.com