“በአራጣ ብድር ሃብታችንን አጣን” የሚሉ ግለሰቦች ያደረሱትን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ባካሄደው ማጣራት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ አብይ አበራ ለበርካቶች አራጣን በማበደር እና ለዚህም የያዙትን ንብረት በመውረሳቸው በአንድ ወቅት ባለሀብት የነበሩ ግለሰቦች ወደ ተመፅዋእችነት መቀየራቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

ይህንንም ዘገባ ተከትሎ ፖሊስ ለረዥም ጊዜ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወቃል።

አራጣ በማበደር ወንጀል የተጠረጠሩት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ አብይ አበራ አሁን ደግሞ ከግለሰብ 1 ሺህ 81 ካሬ ሜትር ቦታን ገዝተው ነገር ግን አጠገቡ የነበረን የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ንብረት የሆነን መጋዘን እና መሬት አጥረው ግንባታ እንዳከናወኑበት ጣቢያችን አረጋግጧል።

ታጥሮ የተያዘው መሬት 2 ሺህ 558 ካሬ ሜትር ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ በግለሰብ ስም የተሰራው ካርታ ግን 1 ሺህ 81 ካሬ ሜትሩን ብቻ የግል ይዞታ ይላል።

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አቧሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ካለው ሰፊ መሬት ውስጥ 1 ሺህ 81 ካሬ ሜትሩን አቶ ብርሃኑ ሃይለሚካኤል በአራጣ ማበደር ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር ላሉት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ አብይ አበራ ሸጡላቸው።

በዚህ ቦታ ላይ አቶ አብይ መኖሪያ ቤት የገነቡ ሲሆን፥ በወቅቱ ቤቱ ካረፈበት መሬት ፊት ለፊት አንድ ሰፊ በቆርቆሮ የተገነባ መጋዘን እና እድሜ ጠገብ ዛፎች እንደነበሩ የራሳቸውን መሬት ብቻ ለአቶ አብይ የሸጡላቸው ግለሰብ ተናግረዋል።

እናም አቶ አብይ በግዥ ካገኙት 1 ሺህ 81 ካሬ ሜትር መሬት ውጪ የቀድሞ የኪራይ ቤቶች የአሁኑ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ንብርት የሆነውን 1 ሺህ 477 ካሬ ሜትር መሬት የግላቸው ማድረጋቸውን ሰነዶች ያሳያሉ።

ግለሰቡ ይህንን ግንባታ ሲያከናውኑና የመንግስትንና የህዝብን ሀብት የግላቸው ሲያደርጉ የይዞታው ባለቤት የፌድራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያውቀው ጉዳይ አለመኖሩን ገልጿል።

በኮርፖሬሽኑ የቤቶች አስተዳደር ተወካይ ሃላፊ አቶ ታደሰ ገልሜሳም ጉዳዩን እንደማያውቁት ተናግረዋል።

ይሁንና ለኮርፖሬሽኑ “ንብረታችሁ ተዘርፏልና አጣሩ” የሚል ጥቆማ ቀርቦ እንደነበር ተገልጿል።

አቶ ታደሰ ከሁለት ወር በፊት ጉዳዩ ይዞታውን በሚያስተዳድረው የኮርፖሬሽኑ አካል በሆነው ቅርንጫፍ አራት እንዲጣራ ትዕዛዝ ሰጥቼ ነበር ቢሉም የቀጠናው ሃላፊ ግን ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።

አቶ አብይ አጥረው ግንባታ ያካሄዱበትን የኮርፖሬሽኑን መሬት እንዲያይ ከኮርፖሬሽኑ የተላከው ሰራተኛ በአቶ አብይ ቤት ጥበቃ አትገባም ተብሎ ተመልሷል።

ኮርፖሬሽኑ ንብረቱንና ይዞታውን የማስጠበቅ፤ መጋዘኑንም የመጠበቅ ብቻም ሳይሆን መጋዘኑን እንዲጠብቁ የቀጠራቸው የመሬቱ የቀድሞ ባለይዞታ አቶ ብርሃኑ እና የአካባቢው ነዋሪ ድሮ ነበሩ ስለሚሏቸው የራሱ የጥበቃ ሰራተኞች እንኳን ምንም መረጃ የለውም።

አቶ ታደሰ የጥበቃ ሰራተኞቻችን አሉ ቢሉም የጥበቃ ሰራተኞቹ እንደተባረሩ ምን ያህል ታውቃላችሁ ተብለው ቢጠየቁም መረጃው የለንም ብለዋል።

በቅርጫፍ አራት ቁጥጥር ስር ነው የተባለው መጋዘን በአቶ አብይ ጊቢ ውስጥ ገብቶ መሬቱም ታጥሮ ተይዟል።

22.png

ይሁንና ከ2 ሺህ 558 ካሬ ሜትር ቦታ ውስጥ 1 ሺህ 81 ካሬ ሜትሩ የአቶ አብይ ይዞታ መሆኑን የሚገልፀው ካርታ ሲገኝ ቀሪው 1 ሺህ 477 ካሬ ሜትር ቦታ የኮርፖሬሽኑ መሆኑን የሚገልፀው ካርታ አልተገኘም።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሃብታሙ ጥላሁንና ምክትላቸው አቶ ይርጋዓለም ኩመሌ ይህንን በተመለከተ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ መሸሽን መርጠዋል።

በኮርፖሬሽኑ የቤቶች አስተዳደር ተወካይ ሃላፊ አቶ ታደሰ ካርታውን ፈልገን አላገኘንም ብልዋል።

ካርታው በኮርፖሬሽኑ መዝገብ ቤት ቢፈለግም የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ ካርታው ባይሰራ እንጂ ይገኝ ነበር ይላሉ።

የቅርንጫፍ አራት ሰራተኛ ግን ካርታውን እኔ ራሴ ቆሜ አሰርቻለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

ይዞታቸውን ለአቶ አብይ የሸጡት አቶ ብርሃኑ ግን የኮርፖሬሽኑ ይዞታ መረጋገጫ ካርታ የሳቸው ከመሰራቱ በፊት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የአቶ ብርሃኑ ካርታ የተሰራው በ2007 ዓመተ ምህረት ነው፤ በዚህ መሰረት የኮርፖሬሽኑ ካርታ የተሰራው ከዛሬ ሁለት ወይም ሶስት አመት በፊት ነው ማለት ነው።

ካርታው በኮርፖሬሽኑ እጅ አለመገኘቱ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ ጉዳዩን ከህግ ውጭ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉበት ያመለከተ ነው ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ አሁንም ካርታውን እያሰሰ መሆኑን በመግለጽ ዛሬ ይገኛል እያለ ሲሆን፥ የታጠረውን ግንብ የማፍረስ ስራም ይጀመረል ብሏል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ተገኑ ጉዳዩ ተጣርቶ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

ካርታው ዛሬ ይገኛል ስለተባለ ጉዳዩን በተመለከተ ከኮርፖሬሽኑ የምናገኘውን መረጃ እናደርሳለን።

33.png

በዳዊት መስፍን