ደቡብ አፍሪካዊው የፀረ አፓርታይድ ታጋይ አህመድ ካትራዳ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ተሰማ።

በፀረ አፓርታይድ ትግሉ ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉት አዛውንቱ ካትራዳ፥ በዛሬው እለት በጆሃንስበርግ ህልፈታቸው ተሰምቷል።

በርካታ ደቡብ አፍሪካውያንም ትልቁን የነጻነት መሪ አጣን ሲሉ ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

የነጻነት ታጋዩ አህመድ ካትራዳ፥ የቀድሞው የነጻነት ታጋይ እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የቅርብ ወዳጅ እንደነበሩ ይነገራል።

በ19 50ዎቹ መጀመሪያ ከነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ጋር በመገናኘት ፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴን አሃዱ ብለው ጀምረውታል።

አህመድ ካትራዳ የነጮችን ጭቆና በመቃወማቸው ሳቢያም በሮቢን ደሴት እና ፖልስሞር 26 አመታትን በእስር አሳልፈዋል።

ለደቡብ አፍሪካ ነጻነት የታገሉት ካትራዳ፥ ባደረጉት የፀረ አፓርታይድ ዘመቻ በፈረንጆቹ 19 52 ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የ9 ወራት የእስር ቅጣትን ተቀብለዋል።

ከአራት አመት በኋላ ከወዳጃቸው ማንዴላ እና ከሌላው የነጻነት ታጋይ ዋልተር ሲሱሉ ጋር በመሆን ከቀረበባቸውና ከፍተኛ ቅጣት ከሚያስከትለው ወንጀል ነጻ መውጣታቸውም ይታወሳል።

anti-apartheid_activist.jpg

የነጻነት ታጋዮቹ ማንዴላ እና ካትራዳ በኋለኛው ዘመን

ከዘጠኝ አመታት በኋላ መንግስትን ለመጣል አሲራችኋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ፥ ከሌሎች ስምንት የነጻነት ታጋዮች ጋር የእድሜ ልክ የእስር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

ኔልሰን ማንዴላ፣ ዋልተር ሲሱሉ፣ ጎቫን ምቤኪ፣ ራይሞንድ ምላባ፣ ዴኒስ ጎልድበርግ፣ አህመድ ካትራዳ፣ አንድሬው ምላንጌኒ እና ኤሊያስ ሞትሷለዲ በወቅቱ የእድሜ ልክ እስራት የተወሰነባቸው የጊዜው ወጣት የነጻነት ታጋዮች ነበሩ።

በወቅቱም ፍርደኞቹ የዘር ቀለማቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ያገኙት የነበረውን የተሻለ የእስር ቤት እንክብካቤ አልቀበልም በማለት ተቃውመዋል።

በጊዜው ነጭ እስረኞች ከህንዶች እና ከጥቁሮች የተሻለ እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር።

ካትራዳ ደግሞ ከህንዳውያን ቤተሰቦች በመገኘታቸው ከጥቁሮች ከፍ ባለ መልኩ እንክብካቤ የማግኘት እድሉ ነበራቸው፤ ከትግል አጋሮቸ አልለይም በማለት ተቃወሙት እንጅ።

ከዚያም ከ26 አመታት በኋላ ከእስር ተለቀው፥ አሁን ላይ ሃገሪቱን የሚመራውን የኤ ኤን ሲ ፓርቲን ተቀላቅለዋል።

ካትራዳ ከአምስት አመት በኋላ በተካሄደውና የሃገሪቱ የመጀመሪያ በሆነው ዴሞክራሲያዊ ምርጫም በሃገሪቱ ፓርላማ አባል በመሆን ተመርጠዋል።

እስከ ፈረንጆቹ 19 99 ድረስም የፕሬዚዳንት ማንዴላ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው አገልገለዋል።

ከ19 97 እስከ 2006ም በእስር ያሳለፉበት የሮቢን ደሴት ሙዚየም ካውንስልን በሊቀ መንበርነት መርተውታል።

የተነሱበት አላማ ዘረኝነትን ማስወገድ ነበርና፥ ዘረኝነትን በማጥፋት አንድነትን የሚሰብከውን አህመድ ካትራዳ ፋውንዴሽንን አቋቁመዋል።

የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የመንግስትን ንብረት መዝብረዋል ተብለው በተወነጀሉ ወቅትም፥ የፓርቲያቸውን አባልና የሃገሪቱን መሪ ነቅፈው ጽፈዋል።

ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጅ መጠቀሚያ አይደለም በሚልም፥ ፕሬዚዳንቱ ስልጣናቸውን ለህዝብ መገልገያ ብቻ ይጠቀሙ ዘንድ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።

ከህንዳውያን ቤተሰቦች የተወለዱት ካትራዳ በጭንቅላት ደም መርጋት ሳቢያ፥ በ87 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ደቡብ አፍሪካም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እና የነጻነቱ ታጋዩ ካትራዳ፥ እለተ ቀብር እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ሰንደቅ አላማዋ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጋለች።

የ91 አመቱ አንድሬው ምላንጌኒ እና የ83 አመቱ ዴኒስ ጎልድበርግ፥ በህይዎት የሚገኙ ብቸኛ የ19 50ዎቹ የነጻነት ታጋይና የፀረ አፓርታይድ ዘመቻ መስራቾች ናቸው።

አህመድ ካትራዳ በትዳር ዘመናቸው ስድስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፥ የቀብር ስነ ስርዓታቸው በእስልምና እምነት መሰረት እንድሚፈጸም ይጠበቃል። ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ