በሰሜናዊ ቻይና በሰርጉ እለት የጋበዛቸው 200 እንግዶች በትክክልም ዘመድ ወዳጆቹ እንዳልሆኑ በሚስቱ ቤተሰቦች የተደረሰበት ሙሸራ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በሻንሺ ግዛት የሚገኝ አንድ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው የሙሽራዋ ቤተሰብ የሆነ ሊዮ የተባለ ሰው ከሙሽራው ወገኖች ጋር ያደረገው የቃላት ልውውጥ እንዲጠራጠር አድርጎታል።
ሊዮ ስለ ሙሽራው እና እነርሱ ግንኙነት ሲጠይቃቸው “ጓደኛ ነን” ከማለት ባለፈ ስለ ሙሽራው የሚያውቁት ዝርዝር መረጃ እንደሌለም ይረዳል።
የሰርግ ስነ ስርአቱ ሲጀመርም የሙሽራው ወላጆች እና ቤተሰቦች አለመታየታቸው ጥርጣሬው እንዲያይል አድርጓል።
ከሻንሺ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰርጉ እድምተኞች፥ ሙሽራው በሰርጉ እለት እንደ ቤተሰብ እና ጓደኛ በመተወን እንዲውሉ ለእያንዳንዳቸው 80 የቻይና ዩዋን (12 የአሜሪካ ዶላር) እንደከፈላቸው ተናግረዋል።
ከእድምተኞቹ መካከል የታክሲ ሾፌሮች እና ተማሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፥ አንድ ዊቻት የተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ ተጠቃሚም በሰርጉ ላይ ለመታደም ከሙሽራው ለቀረበለት ጥያቄ ያደረገውን የዋጋ ድርድር የሚያሳይ የመልዕክት ልውውጥ ይፋ አድርጓል።
ጥንዶቹ ለሶስት አመታት በፍቅር ያሳለፉ ሲሆን፥ ሙሽራው ይህን ተግባር የፈጸመበት ምክንያት ግልፅ አይደለም ተብሏል።
ሙሽራው የተላለፈው የሀገሪቱ የሰርግ ህግም አልተገለፀም።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ሙሽራው “ድሃ” በመሆኑ የሙሽራዋ ቤተሰቦች በጋብቻው አልተስማሙም፤ በመሆኑም ቤተሰቦቹን በሰርጉ ጠርቶ ከማሸማቀቅ ይልቅ ሰዎችን በገንዘብ መግዛትን መርጧል የሚል ዘገባ አውጥተዋል።
ይሁን እንጂ “ለ200 እድምተኞች ወደ 1600 ሺህ ዩዋን (2 ሺህ 400 የአሜሪካ ዶላር) የከፈለው ሙሽራ እንዴት “ድሃ” ይባላል”? ፤ “ምናልባትም ሌላ የሚያሳፍር ችግር ገጥሞት ሊሆን ይችላል” የሚሉ እና ሌሎች ሀሳቦች በቻይናው ሲና ዌይቦ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተጠቅሰዋል።
ሺቡ ኦንላይን የተሰኘ የዜና ወኪልም ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ ነው ብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ