ስኬታማ ከናንተ ብትርቅም ተስፋ አትቁረጡ፤ ሞክሩ፣ ሞክሩ፣ ሞክሩ… ይላል ለ25 አመታት የመንጃ ፈቃድ ፈተናዎችን ማለፍ ያልቻለው ጎልማሳ።
ክርስቲያን ዊትሊይማሶን ይሰኛል፤ ባለፉት 25 አመታት 33 የመንጃ ፈቃድ ፈተናዎችን ወስዷል።
14 የተለያዩ አሰልጣኞችንም ቀያይሮ ፈተናውን ለማለፍ ሞክሯል።
ክርስቲያን ለሩብ ክፍለ ዘመን 85 የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን ስነ አነዳድ እና የትራፊክ ህጎች የተማረና 10 ሺህ ፓውንድ ያወጣ ቢሆንም ያለመው የመንጃ ፈቃድ እጁ ሊገባ አልቻለም።
በመጨረሻው 33ኛው ሙከራ ግን ክርስቲያን የ25 አመታት ድካሙ ሰምሮለት የመንጃ ፈቃድ ፈተናውን ማለፍ ችሏል።
የ42 አመቱ ጎልማሳ በእንግሊዝ ደቡብ ዮልክሻየር ነዋሪ ሲሆን፥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንጃ ፈቃድ ፈተና የወሰደው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1992 ነበር።
ይህን ፈተናም ማለፍ ያልቻለው ክርስቲያን በተከታታይ ተመሳሳይ ሙከራዎችን ቢያደርግም አልተሳካለትም።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2003 ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱም መንዳት ለእኔ አልተፈቀደም ብሎ እንዲያስብ ምክንያት መሆኑንም ያስታውሳል።
ክርስቲያን 40ኛ አመቱን ሲያከብር ግን የተወሰነ ትምህርት ወስዶ ፈተናውን በድጋሚ ለመውሰድ መወሰኑን ተናግሯል።
ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ታክሲ ለመጠቀም አና ሌሎች ጓደኞቹን ለማስቸገር መገደዱ ፈተናውን ለ33ኛ ጊዜ መሞከር አለብኝ ብሎ እንዲያስብ እንዳደረገውም አመላክቷል።
“ሰዎች ይስቁብኛል፤ አንተ ፈተናውን ማለፍ አትችልም ይሉኛል፤ በዚህም ቅስሜ ቢሰበርም እንደምችል ግን ማሳየት እንዳለብኝ አመንኩ” ይላል ክርስቲያን።
ይህ የዘወትር ፍላጎቱም ተሳክቶ ከ32 ያልተሳኩ ሙከራዎች፤ ከ25 አመታት በኋላ የመንጃ ፈቃድ ፈተናውን አልፏል።
“መፈክሬ ሁሌም የማይቻል ነገር እንደሌለ መሳብ አለብን የሚል ነው” የሚለው ክርስቲያን፥ ምንም እንኳን መሰናክሎች ቢኖሩም ካሰብንበት መድረስ እንችላለን የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል። ምንጭ፦ www.mirror.co.uk/