የእንግሊዝ ተመራማሪዎች የህፃናት የአእምሮ የእድገት ደረጃን የሚያሳይ የመጀመሪያ የሆነውን የምርምር ውጤት ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ ግኝትም በመላው አለም ያሉትን ተመራማሪዎች ጤናማ የአእምሮ የእድገት ሂደትን ማወቅ ያስችላቸዋል ሲሉ ዘ ድቨሎፒንግ ሁማን ኮኔክተም የተሰኘ ፕሮጀክት ባለሙያዎች ተናገረዋል፡፡
ጥልቅ የሆነው የኤም አይ አር የምርመራ ውጤት በአእምሮ ላይ የሚከሰቱ የአዕምሮ መዛባቶችንና ኦቲዚምን ይበልጥ ማወቅ ያስችላል ብለዋል፡፡
ግኝቱ እነዚህ በአእምሮ ውስጥ የሚገኙና በቢልየኖች የሚገኙ ውስብስብ የአእምሮ ክፍሎችንም መለየት ያስችላል ተብሏል፡፡
ከ ለንደን ኪንግስ ኮሌጅ ኢምፔሪያል ኮሌጅ እና ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰባሰቡ የጥናት ቡድኖች እንደሚሉት ይህ የምርምር ውጤት እጅግ አስቸጋሪ እና እልህ አስጨራሽ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
የጨቅላ ህፃናት አእምሮ በትሪሊየኖች የሚቆጠሩ ቱቦዎችና የደም ስሮች የያዙ ሲሆኑ እስከ አሁንም ከተወለዱ ጥቂት ቀናት ያስቆጠሩ 40 ጨቅላ ህፃናት የተገኙ የአዕምሮ መረጃዎችን ይፋ አድርገዋል፡፡
በቀጣይ የጨቅላ ህፃናትን እንዲሁም ያልተወለደ ፅንስ ሳይቀር ምርመራ በማድረግ ተጨማሪ መረጃዎችን መሰብሰብ ቀጣዩ ስራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህንን ማድረግ ደግሞ የሰው ልጅ የአእምሮ አቀማመጥ በግልፅ ማስቀመጥ ያስችለናል ሲሉ የጥናቱ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ተናግረዋል፡፡
በአእምሮ እድገት ላይ በርካታ መረጃዎችንን መሰብሰብ መቻላችን ጤነኛ የሆነውን እና ያልሆነውን የሰው ልጅን የአእምሮ እድገት ለይተን ማወቅ ያስችለናል ሲሉ ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡
ህፃናት ከውልደት ቀናቸው ቀድመው ሲወለዱ በእዕምሮ ዕድገታቸው ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችልና የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ህፃናት የአእምሮ እድገትም ምን እንደሆነ ቀድሞ በመረዳት መከላከል ያስችለናል ተብሏል፡፡
ጥናቱ በ14.9 ሚሊዮን ዮሮ የአውሮፓውያን የምርምር ምክር ቤት ገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ ጥናቱ ግን አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልግና በቀጣይ ጥቂት አመታት እንደሚጠናቀቅ ቢቢሲ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡ (ምንጭ: ቢቢሲ)