አሜሪካዊቷ እናት አካል ጉዳተኛ ልጃቸው ጋር ትምህርት ቤት በመሄድና ሁሉንም የትምህርት አይነት እኩል በመከታተል ትምህርቱን እንዲያጠናቅቅ በማድረጋቸው የክብር ዲክሪ ተሰጥቷቸዋል።
ጁዲ ኦ ኮነር የተባሉት እኚህ እናት በአካል ጉዳት ምክንያት መፃፍ ለማይችለው ልጃቸው ማርተይ ኦ ኮነር የሚማርበት ክፍል ድረስ በመግባት መምህራኖቹ የሚሰጡትን ጽሁፎች እየጻፉለት ከቻፕማን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በማጠናቀቅ በማስተርስ ዲግሪ እንዲመረቅ ረድተውታል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት እና አሁን ከስራቸው በጡረታ የተገለሉት እናት ጁዲ ባሳለፍነው ቅዳሜ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይም ልጃቸውን በተሽከርካሪ ወንበር እየገፉ ወደ መመረቂያው ስፍራ ወስደውታል።
ማርተይ እንደ አውሮፕዋኑ አቆጣጣር በ2012 የመውደቅ አደጋ ደርሶበት ከትክሻው በታች ያለው የሰውነት ክፍሉ መንቀሳቀስ አይችልም።
ታዲያ መንቀሳቀስ የማይችለውን ልጃቸውን ለማስመረቅ መድረክ ላይ ይዘውት የወጡት እናትም እዛው መድረክ ላይ ድንገት ያልጠበቁት አስደሳች ነገር ያጋጥማቸዋል።
ይህም ልጃቸው ትምህርቱን እንዲያጠናቅቅ የረዱት እናትም ከዩኒቨርሲቲው በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድምኒስትሬሽን የክብር ዲግሪ ተበርክቶላቸዋል።
በምርቃው ላይ መድረክ ሲመራ የነበረው አስተዋዋቂ፥ “እናት ጁዲ ኦ ኮነር ከልጃቸው ጋር ሁሉንም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ገብተው ተከታትለዋል፤ ለልጃቸው ፅሁፍ ከመጻፍ ጀምሮ በሁሉንም የትምህርት እንቅስቃሴው አግዘውታል” ሲል ተናግሯል።
እናት ጁዲ ኦ ኮነር በበኩላቸው፥ “ልክ ማንኛውም እናት እንደምታደርገው ልጄ በህይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች እንዲያልፍ ነው የረዳውት” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ሁሌም በእሱ እተማመናለው ያሉት” ጁዲ፥ “ልጄ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደሚችልም አውቃለው፤ ዩኒቨርሲቱ ውስጥም ከልጄ ጋር ማጥናት በጣም እወዳለው” ብለዋል።
ከቻፕማን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የተመረቀው ማርተይ ኦ ኮነር፥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ከአውሮፕላን ደረጃ ላይ ወድቆ ሰውነቱ መንቀሳቀስ ከማቆሙ በፊት በሽያጭ ሰራተኝነት ተቀጥሮ በመስራት ላይ ነበር።
ከዚያ ቀደም ብሎ የበረዶ ሸርተቴ እና የመረብ ኳስ ተወዳዳሪ የነበረው ማርተይ ኦ ኮነር፥ ትምህርቱን በሚማርበት ወቅትም ድምጽ የሚያነብ ሶፍትዌር እና በአፍ የሚያዝ ቀጭን እንጨቶችን ይጠቀም ነበር።
ማርተይ፥ “እናቴ ባገኘችው ክብር በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱ ደግሞ ይህ ይገባታል” ብሏል።
ምንጭ፦ www.bbc.com