የቱሪስቶቹ የጨረቃ ጉዞ የሰው ልጅ ጥልቅ ወደ ሆነው የህዋ ክፍል ሲመጥቅ ከ45 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የስፔስ ኤክስ ዋና ሀላፊ ኤሎን ሙስክ ገልፀዋል፡፡ሀላፊው አክለውም በቀጣዩ አመት መጨረሻ አካባቢ ሁለት ጎብኝዎችን ይዞ ለመጓዝ ዕቅድ እንደተያዘና ቱሪስቶቹም የሚጠበቅባቸውን ክፍያ አብዛኛውን ከፍለው ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡የቱሪስቶቹ ማንነት ለጊዜው ይፋ ያልተደረገ ሲሆን ከአሜሪካኑ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ጋር በመተባበር በዚህ አመት መጨረሻ የሙከራ በረራ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡የስፔስ ኤክስ ዋና ሀላፊ በሰጡት መግለጫ ወደ ጨረቃ የሚጓዙት ጎብኝዎች በቅርቡ የጤና ምርመራ እና የአካል ብቃት ፍተሻ ይጀምራሉ፡፡ተጓዦቹ የሚተዋወቁ ሰዎች መሆናቸውንና ከሆሊውድ ዝነኞች መካከል ግን አለመሆናቸውንም ሀላፊው ገልፀዋል፡፡እንደ አፖሎ ጠፈርተኞቹ ሁሉ የአሁኑ ተጓዦችም የሰው ልጆች ስለ ህዋ ለማወቅና ለመመራመር ያላቸውን ህልምና ተስፋ አንግበው ይጓዛሉ ተብሏል፡፡ጎብኝዎቹ በጨረቃ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ሲሆን በጨረቃ ላይ ማረፍ ግን የጉብኝቱ አካል አለመሆኑ ተገልጿል፡አሜሪካ እኤአ ከ1970ዎቹ ወዲህ ወደ ጨረቃ ጉዞ ስታደርግ የመጀመሪያ እንደሆነ የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ምንጭ፤ ቢቢሲ