አትክልትና ፍራፍሬን አብዝቶ መመገብ ለመላው ጤንነት መልካም መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት የዚህን ጠቀሜታ የተመለከተ ጥናትና ምርምር ይደረጋል።
በአውስትራሊያ የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ምርምር ውጤትም ከሰሞኑ ይፋ ሆኗል።
ጥናቱ አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ ለአዕምሮ ጤናና ጭንቀትን ከማስወገድ አኳያ ያለውን ጥቅም የተመለከተ ነበር።
እናም በቀን አትክልትና ፍራፍሬን አብዝቶ መመገብ ጭንቀትን በተለይም በሴቶች በኩል ለመቀነስ ይረዳል ነው የሚለው የጥናቱ ውጤት።
በጥናቱ እድሜያቸው 45 አመትና ከዛ በላይ የሆኑ 60 ሺህ 404 ወንድ እና ሴቶች ተካተዋል።
ለሶስት አመታትም የሰዎቹ አመጋገብ በየቀኑ የተፈተሸ ሲሆን፥ በቀን ምን ያክል አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚመገቡም ተለይቷል።
በእነዚህ ጊዜያት ታዲያ የሰዎቹ የስነ ልቦና ጥንካሬ እና የጭንቀት እና ድብርት መጠናቸውም ተለክቷል።
በጥናቱ ማብቂያ ላይ ታዲያ በቀን ከሶስት እስከ አራት የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚመገቡት፥ ከማይመገቡት ይልቅ ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው በ12 በመቶ ያነሰ ነው ተብሏል።
በቀን ከአምስት እስከ ሰባት አይነት አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚገቡት ደግሞ፥ ከማይመገቡት ይልቅ በ14 በመቶ ለጭንቀት እና ድብርት የመጋለጥ እድላቸው ዝቅ ያለ ነው።
ይህ ሁኔታ በጾታ ስብጥር ሲታይ ደግሞ ውጤቱ ሴቶች ላይ የጎላ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
እናም በዛ ያለ አትክልት ፍራፍሬ የተመገቡት ሴቶች ከማይመገቡት በተሻለ ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው በጣም አናሳ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በዚህም እስከ ሰባት አይነት አትክልት እና ፍራፍሬ የተመገቡት ከማይመገቡት ወይም አንድ አይነት ብቻ ከሚመገቡት ይልቅ ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው በ23 በመቶ ያነሰ ነው።
በቀን ሁለት አይነት የሚመገቡት ደግሞ በ16 በመቶ፥ እንዲሁም ሶስት እና አራት አይነት አትክልትና ፍራፍሬ የሚመገቡት ከማይመገቡት ይልቅ በ18 በመቶ ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው አነሳ ነው።
በቅርብ ጊዜያት በተደረጉ ጥናትና ምርምሮች በቀን እስከ ሰባት አይነት አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ ለስነ ልቦና ጥንካሬ እንደሚረዳ መገለጹ ይታወሳል።
ተመራማሪዎቹም ታዲያ እነዚህ ምግቦች ከጭንቀትና ከስነ ልቦና ጋር ያላቸውን የተለየ ዝምድና የተመለከቱ ተጨማሪ ጥናትና ምርምሮች እያደረጉ መሆኑም ተነግሯል።
ምንጭ፦ medicalnewstoday.com