የጃፓን መንግስት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የእድሜ ባለጠጎች የመንጃ ፈቃዳቸውን እንዲመልሱና ማሽከርከር እንዲያቆሙ በመጠየቅ ላይ ነው።
ለዚህም ይመስላል አዛውንቶች ማሽከርከር ካቆሙ ወይንም መንጃ ፈቃዳቸውን ከመለሱ የቀብር ማስፈፀሚያ ወጪያቸው ላይ ቅናሽ ይደረግላቸዋል የተባለው።
በማዕከላዊ ጃፓን አይቺ ግዛት ነው አንድ 89 የመቃብር ቤቶችን የሚያስተዳድረው ኩባንያ የመንጃ ፈቃዳቸውን ለሚመልሱ አዛውንቶች የ15 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን ያስታወቀው።
ኬይዶ የተባለ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው፥ ማንኛውም መንጃ ፈቃዱን መመለስ የሚፈልግ የእድሜ ባለጠጋ በአካባቢው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ በማመልከት የቅናሹ ተጠቃሚ መሆን ይችላል ተብሏል።
ቅናሹ የማዕከላዊ አይቺ ግዛት ነዋሪ ያልሆኑ ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው በዚያው የሚገኙ ሰዎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 በጃፓን ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የመንጃ ፈቃድ ባለቤቶች እድሜያቸው ከ75 አመት በላይ መሆኑ ተደርሶበታል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አዛውንቶች መንጃ ፈቃዳቸውን እንዲመልሱ ከላይ እንደጠቀስነው ያሉ ማበረታቻዎች ቢቀርቡም በሚፈለገው ልክ ማሽከርከር አላቆሙም።በአይቺ ግዛት ከመቃብር ቤት ዋጋ ቅናሹ በፊት ሌላ ማበረታቻ ቀርቦ እንደነበር ተጠቁሟል።
ባለፈው ህዳር ወር ይፋ በተደረገው ማበረታቻ መንጃ ፈቃዳቸውን የሚመልሱ አዛውንቶች በግዛቲቱ በሚገኙ ማንኛውም ምግብ ቤቶች ራመን የተባለውን ምግብ ሲመገቡ የ15 በመቶ ቅናሽ እንዲደረግላቸው ከስምምነት ተደርሶ ነበር።
በጃፓን በአዛውንት አሽከርካሪዎች የሚደርሱ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ይነገራል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ