በናይጄሪያ በሰሜን ምስራቅ ክፍል በቦርኖ ግዛት ከሚገኘው ከቺቦክ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 276 ሴት ተማሪዎች በአሸባሪው ቦኮሃራም ታግተው ከተወሰዱ ድፍን ሦስት ዓመት ሊሞላ አንድ ወር ብቻ ይቀራል ፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሚያዚያ ወር መባቻ ላይ አሸባሪ ቡድኑ ኮረዳዎቹን አግቶ ወዳልታወቀ ሥፍራ መውሰዱን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን በጥብቅ አውግዞታል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ግለሰቦች ልጃገረዶቹ ከእገታ እንዲለቀቁ እና የመማር መብታቸው እንዲከበር ቅስቀሳዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል ፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደረጉት የማስለቀቅ ዘመቻዎች 81 ልጃገረዶችን ብቻ ማስለቀቅ የተቻለ ሲሆን ፣ 195ቱ ግን እስካሁን እንደታገቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ሦስት ዓመት ሊሞላ ነው ፡፡
ቢቢሲ ሰሞኑን ለንባብ ያበቃው ዘገባ እንዳመለከተው ፣ ለደህንነቷ ሲባል በዚህ ዘገባ ስሟ ያልተጠቀሰው እና ‹‹ሳ›› በሚል የተጠቀሰችው ኮረዳ አባቷና ወንድሟ በቦኮሃራም ከተገደሉባት ጓደኛዋ ጋር በመሆን ሰሞኑን በዱባይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ላይ ተገኝተው ቦኮሃራም በልጃገረዶቹ ላይ የፈጸመውን ተግባር አብራርተዋል ፡፡
‹‹ሳ›› ይህ አረመኔያዊ ተግባር በልጃገረዶቹ ላይ በተፈጸመበት ወቅት የቺቦክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበረች ፡፡ በዕለቱ ቦኮሃራም ትምህርት ቤቱ ገብቶ ካገታቸው ተማሪዎች አንዷም ነበረች ፡፡ ቦኮሃራም በዕለቱ መጽሐፍትን እና መማሪያ ክፍሎችን ካቃጠለ በኋላ በሴት ተማሪዎች ላይ መሳሪያ ደቅኖ ወደ ጭነት መኪናዎች አስገባቸው ፡፡
መኪናው በጫካ ውስጥ እየተጓዘ ሳለ ሳ እና ጓደኛዋ ከመኪናው በመዝለል ያመልጣሉ ፡፡ ሌሊቱን በሙሉ ጫካ ውስጥ ተደብቀው ያሳልፋሉ፡፡ በእረኞች እገዛም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ ሳ በዚያን ምሽት ከመኪናው ለመዝለል ባትወስን እስካሁን ድረስ በግዞት ልትኖር ትገደድ እንደነበር እና ከቤተሰቦቿ ጋር መገናኘት እንደማትችልም ታስታውሳለች፡፡
ስለ ታገቱት ጓደኞቿ ሳ ‹‹የጠፉት ሴት ልጃችሁ ወይም ሚስታችሁ ቢሆኑ ምን ሊሰማችሁ እንደሚችል አስቡ፣ ለአንድ ቀን ወይም ለሁለት ቀናት አይደለም፣ ለሦስት ዓመታት ነው እነዚህ ልጃገረዶች የታገቱት ፣ በጣም ከባድ ነው›› በማለት ለጉባዔው ተሳታፊዎች አብራርታለች ፡፡
ከታገቱት መካከል እስካሁን የተለቀቁት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስም አሁንም ድረስ በቦኮሃራም እገታ ስር የሚገኙትን ሴቶች ‹‹ትልቅ ቦታ የመድረስ ህልም የነበራቸው ፡፡ አሁን ግን ህልማቸው የጨለመ›› ስትል ገልጻቸዋለች ፡፡
‹‹የታገቱት ሴቶች የሰው ዘር ናቸው፣ ዝም ብለን ልንረሳቸው አይገባም ››ያለችው ሳ ፣ ልጃገረዶቹን ለማስለቀቅ እና ትምህርት ቤቶችን ከእንደዚህ ዓይነቱ ጥቃት ለመከላከል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቻለውን ማድረግ እንዳለበትም አሳስባለች ፡፡
ሳ እንደገለጸችው በልጆቻቸው መታገት ምክንያት በድንጋጤ በርካታ ወላጆች ህይወታቸውን አጥተዋል ፣ ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸው ከዛሬ ነገ ይመለሳሉ ሲሉ ቆይተው ተስፋ በመቁረጥ ለአዕምሮ ህመም ተዳርገዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ እንደ አውሮፓ ውያኑ ዘመን ቀመር ከ2009 ጀምሮ የሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ክፍልን የተቆጣጠረው ቦኮሃራም ባለፉት 18 ዓመታት 20 ሺ የዚያች አገር ዜጎችን ገድሏል፤ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑትን ደግሞ ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፡፡ ቡድኑ አሁንም ቢሆን አጥፍቶ ጠፊዎችን በማሰማራት በአገሪቱ ከተሞች የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት መንጠቁን ቀጥሏል ፡፡
ዜጎች እና በአገር ላይ ይህን ያህል ግፍ የፈጸመውን ቡድን የናይጄሪያ መንግሥት ለመደምሰስ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ዘመቻ ቢያደርግም ቡድኑ ከቺቦክ ትምህርት ቢት አፍኖ የወሰዳቸውን ልጃገረዶች ግን መታደግ አልቻለም፡፡ ለምን ይሆን፡፡
የአፍሪካ ደህንነት ልዩ ባለሙያ የሆኑት ሪያን ካሚንግስ ለሲ ቢ ሲ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፣ ‹‹የናይጄሪያ መንግሥት ልጃገረዶቹን ለማስለቀቅ የሚደረጉ ወጊያዎች በአገሪቱ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ያስከትላል›› በሚል ስጋት እስካሁን ጠንካራ እርምጃ አልወሰደም፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ መንግሥት በቡድኑ የወሰደው እርምጃ አናሳ ነው በሚል ትችት አስከትሏል ይላሉ፡፡
ልዩ ባለሙያው እንደሚሉት፣ ሴቶቹን ለማስለቀቅ የናይጄሪያ መንግሥት ከቡድኑ ጋር መደራደር ብቸኛው አዋጭ አማራጭ ነው፡፡ ሴቶቹን ለመልቀቅ ከናይጄሪያ መንግሥት ገንዘብ ማግኘት እና የታገቱ የቡድኑ የጦር መሪዎችን ማስለቀቅ የቡድኑ ዋና ዓላማዎች ናቸው፡፡
የአገሪቱ መንግሥት ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን በአገሪቱ መንግሥት እና በቡድኑ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት በዚህች አገር ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት አያባራም፡፡እልቂትም የሚቀጥል ይሆናል ፡፡
ልዩ ባለሙያው ይሁን የበሉ እንጂ ሴቶቹን ለማስለቀቅ ገንዘብ መክፈል እና የቡድኑን የጦር መሪዎች መልቀቅ በቀድሞውም ይሁን በአሁኑ የናይጄሪያ መሪዎች ዘንድ ተቀባይነትን ያላገኘ ሃሳብ ነው፡፡ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድ ላክ ጆናታን መንግሥት ከአሸባሪ ቡድን ጋር መደራደር እንደማይፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የአሁኑ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ በትረ ስልጣን በያዙበት ወቅት የታገቱ የችቦክ ትምህርት ቤት ሴቶችን እና ሌሎች በቡድኑ የታገቱ ንጽሃን ዜጎችን ከቡድኑ ቁጥጥር ሳያስለቅቅ መንግሥታቸው ቦኮሃራምን ድል መምታት እንደማይችል ቢያስታውቁም ልጃገረዶቹ ዛሬም ድረስ እንደታገቱ ናቸው ፡፡
በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ እና የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ትንታኔ የሚሰጠው ዓለም አቀፉ መንግሥታዊ ያልሆነው የቀውስ አስወጋጅ ቡድን በትንታኔው፣ የጆናታን መንግሥት ለታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ ግዴለሽ ነበር ሲል ተችቶታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሴቶቹ አልታገቱም በማለት ክዶ እንደነበርም ነው ያመለከተው ፡፡ ጉዳዩ መከሰቱን ካመነ በኋላም ቢሆን ሴቶችን ለማስለቀቅ አቅም እንዳልነበረው ነው ያብራራው ፡፡
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኮረዳዎቹን ለማፈላለግ ብዙ ጥረቶችን ያደርግ እንደነበር ነው ያስታወሰው፡፡ የናይጄሪያን ጦር መፍረክረክ እና ቅንጅት ማጣት እንዲሁም በአገሪቱ ጦር ወስጥ ያለውን ክፍፍል ምክንያት በማድረግ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥረት ፍሬያማ እንዳይሆን አድርጓል ሲል የአገሪቱን መንግሥት እና መከላከያ ኃይል ተችቷል፡፡