በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ግንኙነት ዙሪያ በተቀረፁ ፖሊሲዎች ውስጥ በመግባትና ቡድን በማዋቀር ሠርተዋል፡፡ ካርኒጊ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ ውስጥ ከ34ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዲዋይት አይዘንአወር፣ ከአይቢኤም ፕሬዚዳንት ቶማስ ዋትሰን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ለመመሥረት ከተሳተፉትና በኋላም ለቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሰልለዋል ከተባሉት የአሜሪካ ባለሥልጣን አልገር ሄስ፣ እንዲሁም ከ52ኛው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ፎስተር ዳላስ ጋር በመሆን በቦርድ አባልነት አገልግለዋል፡፡
በአሜሪካ ከታዋቂው የንግድ ሰው ሶል ሊኖውትዝና ከሌሎችም ጋር በመሆን በደሃ አገሮች ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣትና የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት፣ ለትርፍ የማይሠራውን ዓለም አቀፍ ኤግዙኪዩቲቭ ሰርቪስ ኮርፕ ካቋቋሙዋቸው ድርጅቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡በአገራችን አንድ ሰው ገንዘብ ካለውና ሲበትን ከተስተዋለ ‹‹ሮክፌለር ነው!›› እንደሚባለው ዓይነት ሳይሆኑ፣ የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ የሚሰናዱ ፕሮጀክቶችን የሚረዱ ቢሊየነር ነበሩ፡፡ ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ የዕድሜ ባለፀጋው ቢሊየነር ዴቪድ ሮክፌለር በ101 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
በኒውዮርክ ፖንታንቲኮ ሒልስ በሚገኘው ቤታቸው ተኝተው በነበሩበት ወቅት በዚያው ለዘለዓለሙ ያሸለቡት ሮክፌለር፣ በአሜሪካ ዝናን ካተረፈ ቤተሰብ የተገኙ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1870ዎቹ በኦሃዩ የተመሠረተውን ‹የስታንዳርድ ኦይል›› መሥራች የጆን ዲ ሮክፌለር የልጅ ልጅም ናቸው፡፡የቤተሰባቸውን ንግድና የበጎ ፈቃድ ሥራ አጣምረው የመሩት ሮክፌለር፣ ከስድስቱ የጆን ዲ ሮክፌለር ጁኒየር ልጆች ትንሹ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1936 ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሲሆን፣ በ1940 ደግሞ ከቺጋጎ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ፎርቢስ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ዴቪድ ሮክፌለር ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲያርፉ፣ 3.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ነበራቸው፡፡ በዓለም ካሉ ሀብታሞችም 604ኛ ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡
የሮክፌለር ቤተሰቦች ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ የሮክፌለር ቅድመ ቤተሰቦች እ.ኤ.አ. በ1720ዎቹ ነበር የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ስደተኛ ሆነው ከባቫሪያ ወደ አሜሪካ የገቡት፡፡ ቅድመ ቤተሰቦቻቸው አሜሪካ ከገቡ ከሁለት ምዕተ ዓመት በኋላ፣ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የአሜሪካ መከላከያ ኃይል የደኅንነት ሠራተኛ በመሆን በሰሜን አፍሪካና በፈረንሣይ ሠርተዋል፡፡ ቼስ ናሽናል ባንክንም ለዓመታት መርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1961 የባንኩ ፕሬዚዳንት በኋላም በ1969 ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ቢሊየነር ባይሆኑ እንኳን በዓለም ከሚገኙ መልካም ሰዎች አንዱ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሮክፌለር፣ በኒውዮርክ ከሲቪል እስከ መከላከያ ብሎም በንግዱ ዓለም ረዥም ዕድሜ በመሥራት ከቀዳሚዎቹ የሚመደቡ መሆኑን የኒውዮርክ ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ ተናግረዋል፡፡
ለአሜሪካ ምርቶች በውጭው ዓለም ገበያ መፍጠር ይቻላል በማለት የሚሞግቱ ታዋቂ የካፒታሊስት ንድፈ ሐሳብ አቀንቃኝም ነበሩ፡፡ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እንዲሁም በቻይና የአሜሪካ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከፈትም አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1956 ተከስቶ ከነበረው የስዊዝ ካናል ቀውስ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1974 በግብፅ የመጀመሪያው የባንኩ ቢሮ እንዲከፈት ከማድረጋቸው በተጨማሪ፣ በኒውዮርክ የተዘረጋውን የዓለም የንግድ ማዕከል ፕሮጀክት ከጀርባ ሆነው ሲመሩም ነበር፡ እ.ኤ.አ. በ1981 ላይ 65ኛ ዓመታቸውን አክብረው ጡረታ የወጡት ሮክፌለር፣ በጣም ለጋስ ከሚባሉ ባለሀብቶች የሚመደቡ ናቸው፡፡
ላበረከቱት በጎ ሥራም በአሜሪካ ለከፍተኛ የሲቪል ክብር ከፕሬዚዳንቱ የሚሰጠውን የፍሪደም ሜዳልያ እ.ኤ.አ. በ1998 ማግኘታቸው ይጠቀሳል፡፡
ሮክፌለር በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈው አያውቁም፡፡ ሆኖም በሕይወት ዘመናቸው በአሜሪካ የተመረጡ ፕሬዚዳንቶችን ይመክሩ ነበር፡፡ አሜሪካን እ.ኤ.አ. ከ1977 እስከ 1981 የመሩት 39ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር እንዲሆኑ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉም ነበር፡፡ በ1968 ጆንኤፍ ኬኔዲ ሲገደሉ፣ በሴኔቱ የእሳቸውን ቦታ እንዲተኩ በወንድማቸው ኔልሰን ሮክፌለር ቢሾሙም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ታዲያ እኚህ ሰው በፖለቲካው መሳተፍ ባይፈልጉም ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ፡፡
የቤተሰባቸው መልካም ዝናና በንግዱም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወታቸው የፈጠሩት ግንኙነት የአሜሪካን ፍላጎት ከኩባው ፌደል ካስትሮ፣ ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሚካኤል ጎርቫቾቭ፣ ከኢራቁ ሳዳም ሁሴንና ከሌሎች አገሮች መሪዎች ለማጣጣምም እንደ ድልድይ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ሮክፌለር በለጋሽነታቸውም ይታወሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 ለሙዚየም ኦፍ ሞደርን አርትስ 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ለሮክፌለር ዩኒቨርሲቲ 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ለሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ 10 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ለኮሎኒያል ዊሊያምስበርግ አምስት ሚሊዮን ዶላር ለግሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2006 ደግሞ በዕርዳታ ታሪክ ትልቅ የተባለውን 225 ሚሊዮን ዶላር ለሮክፌለር ብራዘርስ ፈንድ ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን፣ ገንዘቡም ዴቪድ ሮክፌለር ግሎባል ዴቨሎፕመንት ፈንድን በመፍጠር የጤና ክብካቤ ተደራሽነትን ለማጠናከር፣ ዓለም አቀፍ ገንዘብና ንግድ ላይ ጥናት ለማካሄድ፣ ድህነትን ለመዋጋት፣ ዘላቂ ልማትን ለመደገፍና በሙስሊምና በምዕራብ አገሮች መካከል የሚደረጉ ውይቶችን ለማጠናከር ለተቀረፁ ፕሮጀክቶች የዋለ ነው፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ እ.ኤ.አ. በኅዳር 2006 ዘገባው፣ በወቅቱ ሮክፌለር ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደለገሱ አስፍሮ ነበር፡፡ ሮይተርስ የሮክፌለር ሞትን ባተተበት ዘገባው ደግሞ፣ ሮክፌለር እስካለፉበት ጊዜ ድረስ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደለገሱ አስፍሯል፡፡
የሮክፌለር የሀብት ምንጭ ከመጀመሪያ የመጣው ከቤተሰባቸው በተለይም አባታቸው ካቋቋሟቸው ንግዶች ሲሆን፣ በኋላ ላይ በግልና በአክሲዮን የሪል ስቴት፣ የሪዞርት፣ የከብቶች እርባታና የሌሎም ንግዶች ባለቤት በመሆን አዳብረውታል፡፡ የተጣራ ሀብታቸው 3.3 ቢሊዮን ዶላር መሆኑም ተገልጿል፡፡ የስድስት ልጆች አባትም ነበሩ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ፎርብስ ሰሞኑን ባወጣው የቢሊየነሮች ሪፖርት፣ የማይክሮ ሶፍት ባለቤት ቢል ጌትስ በ76 ቢሊዮን ዶላር የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር አድርጓቸዋል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በ3.5 ቢሊዮን ዶላር ካለፈው ጥቅምት ወር 3.7 ቢሊዮን ዶላር ሀብታቸው አዘቅዝቀዋል፡፡ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በ2015 እና በ2016 የሀብት መጠናቸው 4.5 ቢሊዮን ዶላር ነበር ተብሏል፡፡