በቅርቡ ይፋ የሆነው በኢትዮጵያውያን የዘረመል አወቃቀር ላይ ያተኮረ ጥናት የኢትዮጵያውያን ዘረመል አወቃቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየታየበት እንደሆነ ያመለክታል፡፡ በጥናቱ መሠረት የሰው ልጆች ፍልሰት ለለውጡ እንደ ምክንያት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ከየመናውያን፣ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካውያን ጋር ተመሳሳይ ዘረመል እንዳላቸው በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ ከሰዎች ፍልሰት ጋር በተያያዘ የዘር መዋሃድ እንደሚፈጠር ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያውያንን የዘረመል አወቃቀር ለውጥም በዚሁ ማብራሪያ መረዳት ይቻላል፡፡
በእንግሊዙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጥምረት የተሠራው ጥናት ከ70 በላይ የሚሆኑ የዘር ምድቦችን ከሚወክሉ 1,142 ኢትዮጵያውያን የዘረመል ናሙና ተወስዶ የተሠራ ነው፡፡ ተመራማሪዎቹ በ300 የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ዘረመል ለናሙና የወሰዱ ሲሆን፣ ለማነፃፀሪያ በአፍሪካና በአሜሪካ፣ በእስያና በአውሮፓ የሚኖሩ 3,359 ሰዎችን ዘረመልም ወስደዋል፡፡ የተመራማሪዎቹ ጥናት መነሻ ናሙናቸው ከተወሰደው ሰዎች መካከል ምን ያህሉ የዘር ግንድ ይጋራሉ? የኢትዮጵያውያን የዘረመል አወቃቀርስ ምን ዓይነት ለውጥ አሳይቷል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ እንደነበር የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪዎች ዶ/ር ጋሬት ሔላንታልና ዶ/ር ሳዮዎ ሎፔዝ ይገልጻሉ፡፡
ተመራማሪዎቹ የጥናታቸውን ውጤት ሐሙስ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲያሳውቁ ዶ/ር ጋሬት ሔላንታል እንደገለጹት፣ በጥናታቸው ያካተቷቸው ሰዎች የቅርብ የሥጋ ዝምድና ባይኖራቸውም የሰው ልጆች ባጠቃላይ የዘር ግንድ ይጋራሉ፡፡ የሰው ልጆች ዘረመል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እንደመሆኑ የዘረመል ናሙና ሲጠና የሰውን ቀደምት የዘር ግንድ ማንነት ለማወቅ ይቻላል፡፡ ዘረመል ሲጠና ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለው ለውጥም ይታወቃል፡፡
በዓለም ላይ የማንኛውም ሁለት ሰዎች ዘረመል ሲጠና 99.5 በመቶ እንደሚመሳሰል ጥናቶች ያትታሉ፡፡ በርካታ ዓመታት ወደኋላ ቆጥረን ከተመሳሳይ የዘር ግንድ በመገኘታችን ዘረመል የምንጋራቸውን ሰዎች በአካል ባናውቃቸውም፣ ዘረመላችን በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች በሙሉ ያዛምደናል፡፡ ይህ ሐሳብ እንደ መነሻ ሆኖ የኢትዮጵያውን ዘረመል አወቃቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ ያሳየውን ለውጥ ለማጥናት ከ4,500 ዓመታት በፊት የነበረ ዘመረል ናሙና ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነዋሪዎችና ከሌሎች አገሮች ጋር ተነጻጽሯል፡፡
ዶ/ር ጋሬት እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ4,500 ዓመታት በፊት ከነበረ ሞጣ የተባለ ሰው ቅሪተ አካል የተወሰደ የዘረመል ናሙና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ተነጻጽሯል፡፡ ከሞጣ የተወሰደው ዘረመል በጥናቱ ከተካተቱት ሰዎች ዘረመል ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያውን ዘረመል አወቃቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ መምጣቱን ያመላክታል፡፡ ከ4,500 ዓመታት በፊት ከነበረው አወቃቀር የዛሬው የተለየ መሆኑ የተገለጸው ከፈረንሣይ፣ ከቻይና፣ ከየመን፣ ከሴራሊዮን፣ ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪካውያን ከተወሰደው የዘረመል ናሙና ጋር ተነፃፅሮ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከሞጣ ጋር የሚመሳሰሉ የዘረመል አወቃቀሮች የሚታይባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም የአሁን ወቅት የኢትዮጵያውያን ዘረመል ጉልህ ለውጦች ይታይበታል፡፡ በደቡብ፣ በሰሜንና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለው የዘረመል አወቃቀር ከየመናውያን ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ በዋነኛነት ከናይጄሪያና ከሴራሊዮን ሰዎች ጋር የዘረመል አወቃቀራቸው ይመሳሰላል፤›› ሲሉ የጥናታቸውን ውጤት አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዘረመል አወቃቀር ላይ ለውጥ እየታየ የመጣበት ምክንያት የሌሎች አገሮች (በዋነኛነት የየመን፣ የናይጄሪያና የሴራሊዮን) ሕዝቦች ወደ ኢትዮጵያ መፍለሳቸው እንደሆነ ዶ/ር ጋሬት ያስረዳሉ፡፡ በገለጻቸው መሠረት፣ ከ100 እስከ 1,600 ዓመታት በፊት የምዕራብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም ከ300 እስከ 3,500 ዓመታት በፊት የየመን ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች በማፍራት የዘር ግንዳቸው እየተሳሰረ መጥቷል የሚል መላምት አለ፡፡
ተመራማሪው የዘር ውህደት በዓለም ላይ ዘመናትን ያስቆጠረ ሒደት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ዘመናዊ ሰው ከ60 ሺሕ እስከ 120 ሺሕ ዓመታት በፊት ከአፍሪካ ሲፈልስ ኒያንደርታልና ዴኒሶቫንሶ ከተባሉ የሰው ዝርያዎች ጋር በዩሬዥያ (በአውሮፓና እስያ) መገናኘታቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሁለቱ የሰው ዝርያዎች አሁን በምድር ላይ ባይኖሩም ከዘመናዊ ሰው ጋር ዘራቸው በመደባለቁ ዘረመላቸው በዛሬው ሰው እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዚህ ምክንያት የዛሬ የሰው ዘር ባጠቃላይ ሁለት በመቶ ዘረመላችንን ከኒያንደርታል ጋር እንጋራለን፤›› ይላሉ፡፡
የኒያንደርታልና ዴኒሶቫንስ ዘረመል ከ60 ሺሕ እስከ 120 ሺሕ ዓመታት በፊት ከአፍሪካ እንደፈለሱ ሰዎች ባልፈለሱት ሰዎች የዘረመል አወቃቀር ሳይታይ ቢቆይም፣ ከአፍሪካ የፈለሱት ወደ አህጉሪቱ ተመልሰው ካልፈለሱት ጋር ሲዋሃዱ ከኒያደርታልና ዴኒስቫንስ ዘረመል ጋር የሚመሳሰል የዘረመል አወቃቀር ተሰራጭቷል፡፡ በጥናቱ በተካተቱት ኢትዮጵያውያን መጠኑ ይለያል እንጂ በሁሉም ውስጥ የኒያንደርታል ዘረመል መገኘቱን ዶክተሩ ያስረዳሉ፡፡ ከፍተኛ የኒያደርታል ዘረመል የታየው በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋርና በአገው ሕዝብ እንደሆነም ያክላሉ፡፡
በገለጻቸው መሠረት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ያሉ ሕዝቦች ከሌሎች የዓለም ክፍሎች በበለጠ የዘረመል መለያየት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን የዘረመል አወቃቀር ልዩነት ለጥናቱ እንዳነሳሳቸውም ይናገራሉ፡፡ የዘመናዊ ሰው መነሻ በሆነችው አፍሪካ ከ120 ሺሕ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ወደ ሌላው የዓለም ክፍል ሲፈልሱ ከአፍሪካ ጥቂት ዓይነት ዘረመል ብቻ በዓለም አሰራጭተዋል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በሚገኘው ዘረመል መካከል ያለው ልዩነት ከተቀረው ዓለም በልጦ የሚታየው አብዛኛው የዘረመል ዓይነት በአህጉሪቱ በመቅረቱ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡
የጥናቱ ሌላው ትኩረት በአንድ የዘር ምድብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን ያህል ዘረመል ይጋራሉ? የሚለው ነው፡፡ የዘር ግንድ በመጋራት ረገድ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ እንዲሁም ሥራቸውም ከግምት ውስጥ ገብቷል፡፡ በግኝታቸው መሠረት፣ በአንድ ብሔር ውስጥ ያሉ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተመሳሳይ ዘረመል የሚጋሩ ሲሆን፣ ከሌሎች ብሔሮች ጋር ግን ልዩነት አሳይተዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ የሙርሲ ብሔር ከሌሎች ብሔሮች ጋር ካላቸው ተመሳሳይነት በበለጠ እርስ በርስ ተመሳሳይ ዘረመል አላቸው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ሆኖም በተለያዩ የዘር ምድቦች ያሉ ሰዎች ተመሳሳይ የዘረመል አወቃቀር የሚያሳዩበት ጊዜ እንዳለም ይናገራሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ሰዎቹ በተቀራራቢ ቦታ ሲኖሩ እንደሆነ ዶክተሩ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ የከምባታ ሕዝብ በአቅራቢያቸው ካሉት የሐዲያና የአላባ ሕዝቦች ጋር የዘር ግንድ ይጋራሉ፤›› ይላሉ፡፡ ሰዎች በአቅራቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ቤተሰብ የመመሥረት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑ የቦታ ቅርበት ለተመሳሳይ የዘረመል አወቃቀር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው እንደሚጠቁም ያክላሉ፡፡
በተቃራኒው ተቀራራቢ ቦታ እየኖሩ የተለያየ የዘረመል አወቃቀር ያላቸው ሰዎች የሚገኙበት አጋጣሚም ሊኖር እንደሚችል ዶ/ር ጋሬት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ረገድ በተመሳሳይ የሙያ መስክ መሰማራት ተመሳሳይ የዘር ግንድ ለመጋራት መነሻ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን የሚያመላክት ውጤት ከጥናታቸው ማግኘታቸውን ያብራራሉ፡፡ ለዚህ ሐሳብ እንደ ማስረጃ ያቀረቡት ከአሪ ብሔረሰብ በብረት፣ በሸክላ ሥራና በሌሎችም ሙያዎች የተሰማሩ ሰዎችን ዘረመል በማጥናት ያገኙትን ውጤት ነው፡፡ በጥናቱ የተካቱት በተመሳሳይ ሙያ የተሰማሩት ሰዎች ተቀራራቢ የዘር ግንድ ይጋራሉ፡፡
እነዚህ ግኝቶቻቸው የሥነ ቃል እውነትነትን በማረጋገጥ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ዶክተሩ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ስለ ሰው ልጆች ቀደምት የዘር ሐረግ ያለው መረጃ አፋዊ ሲሆን፣ የዘረመል አወቃቀርን በማጥናት መረጃው እውነታ ያዘለ መሆኑን ማጣራት ይቻላል፤›› ያሉት ተመራማሪው እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የማጃንግ ሥነ ቃል ነው፡፡ በማጃንግ ሥነ ቃል መሠረት ሕዝቡ ከዛሬይቱ ሱዳን መምጣቱ የሚነገር ሲሆን፣ በተመራማሪዎቹ ጥናት ታሪኩ ዕውን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በተመሳሳይ የሸኪቾ ሕዝብ ከዛሬዋ እስራኤል እንደመጡ በሥነ ቃል ይነገራል፡፡ የዘመረል ጥናቱ በሥነ ቃል የሚነገርለት ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ የተደረገውን ፍልሰት ያረጋግጣል፡፡ ‹‹የዛሬው ሸኪቾ የዘረመል አወቃቀር በዛሬይቱ የመንና ሊቢያ የሚኖሩ ቤተ እስራኤልና አይሁድ ሕዝቦች የዘር ግንድ መገኘቱ ጥናቱ ያመላክታል፤›› ይላሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር እንዳሻው በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥናቱ የሁሉንም ሥነ ቃሎች እውነታነት ያረጋግጣል ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ የሚያረጋግጣቸው የሰው ልጆች የታሪክ ክፍሎች አሉ፡፡ ጥናቱ በዘረመል አወቃቀር ዘርፍ የነበሩ የሚያረጋግጣቸው መላ ምቶች እንዳሉም ያክላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ የጥናቱ ግኝት የኢትዮጵያ ታሪክና የዘረመል አወቃቀር ታሪክ ምን ያህል ይጣጣማል? የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ውጪ ካሉት ሰዎች አንፃር እርስ በራሳቸው ያላቸው ተመሳሳይነት አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባም ያክላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሰው ልጆች መካከል የ95.5 በመቶ የዘረመል ተመሳሳይነት መኖሩ የሰዎችን አንድነት የሚያጎላ በመሆኑ በጥቃቅን ልዩነቶች መከፋፈል እንደማይገባ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ዋናው የ0.5 ልዩነቱ ሳይሆን የ95.5 በመቶ አንድነቱ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ሳይንሳዊ ግኝቶች በሰው ልጆች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዐውድ የሚጫወቱትን ሚናም ይጠቅሳሉ፡፡ የኢትዮጵያውያንን የዘረመል አወቃቀር በተመለከተ የተሠራው ጥናት በሕክምናው ዘርፍ መድኃኒት ለመቀመም ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን የዘረመል አወቃቀር በመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ ለምርምር ተመራጭ ከሆኑት መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡