ሁሉም በሚመቸው መልኩና ብዙሃኑ በተቀበላቸው መንገዶች ተቃራኒ ጾታን ለመሳብ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል።
ቀልድ መቀለድ፣ የተመራጩን ሰው ፍላጎት መሰረት ያደረገ አቀራረብ፣ ስጦታዎች፣ በእግር ጉዞ አጋጣሚን መጠቀምና ሌሎችንም መንገዶች ተጠቅሞ ይህን ለማሳካት የሚደረግ ጥረት ይስተዋላል።
በዚህ መልኩ የፈለጉትን ሰው የራስ ማድረግና አብሮነትን ማዝለቅም ይቻል ይሆናል።
ተመራማሪዎች ደግሞ አንድን ሰው ተፈላጊ እንዳይሆን የሚያደርጉ ያሏቸውን ምክንያቶች እንዲህ ይዘረዝሯቸዋል።
የእንቅልፍ መቆራረጥ፦ ሌሊቱን አሁንም አሁንም ሲባንኑ አድረው እንቅልፍ ሳይጠግቡ ከነቁ ሰዎችን የመማረክና ለእይታ የመሳብ እድልዎ አናሳ ነው።
ከዚህ ጋር በተያይዞ በስዊድን እና ኔዘርላንድስ ባደረጉት ጥናት ተደጋጋሚ የሆነ የእንቅልፍ መቆራረጥ የሚስተዋልባቸው ሰዎች ጤናቸው የተስተጓጎለ እና ሰዎችን የመማረክና የመሳብ እድላቸውም ዝቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
እንቅልፍ ያጡቱ የአይን አካባቢ ማበጥና መቅላት፣ በአይናቸው አካባቢ ጠቆር ያለ ክብ መስመር እንዲሁም የቆዳ ላይ መስመሮች እና ነጠብጣቦችም ይኖራቸዋል።
ይህ ደግሞ የዚያን ሰው ተፈላጊነት በእጅጉ ይቀንሰዋል ይላል የጥናቱ ውጤት።
ተንኮል፦ በሰዎች ዘንድ ብዙም ተቀባይነት የሌላቸውን ባህሪ የተመለከተው ጥናት ደግሞ በቻይና ተደርጓል።
በዚህም የሰዎች ፎቶ “ጨዋ እና ታማኝ” እንዲሁም “ክፉ እና ተንኮለኛ” ከሚል የግርጌ ማስታወሻ ጋር ለተቃራኒ ጾታዎች እንዲቀርቡ ተደርገዋል።
በዚህ ጊዜ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሁለተኛው ምድብ የሰፈሩትን የክፉ እና ተንኮለኛ ሰዎች በምርጫዎች ዘለዋቸዋል። ይህም አንዱ የተፈላጊነትን መግለጫ መንገድ ነው ተብሏል።
ጭንቀት፦ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰባት ሃገራት የተደረገ ጥናትና ምርምር ለጭንቀት የሚዳረጉ ሰዎች በተቃራኒ ጾታ የማይፈለጉ እና ተመራጭነታቸውም ያን ያክል ነው ይላል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ በብዛት በሴቶች ላይ የጎላ ሲሆን፥ ለጭንቀት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ለፍቅር ግንኙነት እምብዛም አይፈለጉም ተብሏል።
እጅግ የበዛ ደስታ እና የኩሩነት ስሜት፦ ደስታ በሴቶች ላይ ሲታይ የተፈላጊነታቸውን መጠን ቢጨምረውም፥ ሁኔታው በወንዶች ላይ ውጤቱ ተቃራኒ ይሆናል።
በአንጻሩ ኩሩ ባህሪ ያለው ወንድ በሴቶች ዘንድ ተፈላጊነቱ ከፍ ማለቱንም የተደረገው ጥናት ያሳያል።
ይህ ሁኔታ በሴቶች ዘንድ ሲሆን ደግሞ የተቀባይነትና የተፈላጊነት መጠናቸውን በእጅጉ ዝቅ እንደሚያደርገው ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ጥናት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን በጥናቱ አሳትፎ አድርጓል።
ከተለያየ ቦታ የተሰባሰቡት እነዚህ ሰዎች በፎቶግራፋቸው የቀረቡላቸውን ሰዎች ምስል በመመልከት ምርጫቸውን አድርገዋል።
በዚህም የወንዶች ምርጫ የሆኑት ሴቶች በጣም ደስተኞች እና የደስታ ስሜት የሚታይባቸው ሆነዋል።
በአንጻሩ ደግሞ ኩሩ የሆኑ ወንዶች የሴቶቹ ምርጫ ሆነው ታይተዋል ነው የተባለው።
ይህ ውጤት ግን በአብዛኛው ከምዕራባውያኑ የአኗኗር ዘይቤ እና ምናልባትም እሳቤ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ሰፋ ያለ እና ሁሉንም አካባቢዎች ያካተተ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያደርጉ ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ጨዋታ አዋቂነት፦ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፥ ጨዋታ አዋቂነት እና ሰዎችን በቀልድ ዘና ማድረግ መቻል አንዱ የተፈላጊነት መለኪያ ነው።
በጨዋታ መሃል ቀልድ እየፈጠሩ ሰዎችን ዘና ማድረግ እና መጫዎት በሁለቱም ጾታዎች በኩል ተፈላጊነትን ከፍ ያደርጋል።
በተቃራኒው አለመጫዎት ደግሞ ላለመፈለግ እና ላለመወደድ ምክንያት ሆኖም ቀርቧል፤ ለዛ ቢስ ከሆኑ አንፈልጋቸውም የጥናቱ ውጤት ነው።
መፍዘዝና ንቁ አለመሆን፦ የሰዎችን ታታሪነትና ጠንካራ የስራ ባህሪን ከተቃራኒ ጾታ ተፈላጊነት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ደግሞ በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ተደርጓል።
በጥናቱ ከሰዎች ጋር ተባብሮ መስራትም ሆነ ቀልጠፍ ብለው ነገሮችን የሚከውኑ ሰዎች በሁለቱም ጾታዎች በኩል ከፍ ያለ ተፈላጊነትን አሳይተዋል።
በአንጻሩ የመፍዘዝ ባህሪ ያላቸውና እና ቀልጠፍ ብለው ነገሮችን የማይከወኑት ደግሞ በጣም ዝቅተኛ ፈላጊ ያላቸው እና ረዳት የለሽ ብቸኛ ሆነውም ተለይተዋል።
ታማኝ አለመሆን፦ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ለማግኘት በሚል መዋሸትና ማስመሰል ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፤ በካናዳ ኦንታሪዮ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናትም የዚህን ውጤት አሳይቷል።
በጥናቱም በርካታ ወንድና ሴቶች የተካተቱ ሲሆን፥ ወጣቶቹ በአዕምሮ የመጠቁና ተቃራኒዎቹ፣ ጥገኛ የሆኑና ራሳቸውን የቻሉ እንዲሁም ታማኞች እና ያልሆኑ በሚል ተመራጮች ቀርበውላቸዋል።
ከዚህ አንጻር የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ምርጫዎች በመራጮቹ ላይ ብዙም ልዩነት አላስከተሉም፥ የጎደለው በሌሎች ነገሮች ሊካካስ የሚችል ነው በሚል።
ሶስተኛውና የታማኝነቱ ጉዳይ ግን የበርካቶችን ወጣቶች ቀልብ የሳበና ትልቁ የመምረጫ መስፈርት ሆኗል።
በዚህም ታማኝ መሆንና አለመዋሸት የወጣቶቹ ምርጫ ሆኗል፤ ዋሾ የሆኑት ተፈላጊነታቸው ዝቅ ብሏል።
የሲጋራ እና የመጠጥ ሱስ፦ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው አመት ማብቂያ ላይ የተደረገው ጥናት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ በርካታ ወጣቶችን ያሳተፈ ነበር።
በጥናቱም የወጣቶቹ አጠቃላይ መረጃ የቀረበ ሲሆን፥ ካላቸው ነገር ባሻገር የመጠጥ እና ሲጋራ ሱሰኝነታቸውም ቀርቧል።
በዚህም ሲጋራ አጫሾች በሁለቱም ጾታዎች በኩል በጣም የወረደ ፈላጊ ያላቸው ሲሆን፥ በተለይም የረጅም ጊዜ አጋርን የፈለጉ ወጣት ወንዶች አጫሽ ሴቶችን አግልለዋቸዋል።
በአንጻሩ ደግሞ በጣም ጠጭ እና መጠጥ አዘውታሪ የሆኑት ወንድም ሆኑ ሴቶች ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ የፍቅር ግንኙነት የማይፈለጉ ሆነዋል።
ትሁት አለመሆን፦ ትዕቢት አዘል ባህሪና ትሁት መሆን ከፍቅር ግንኙነት ጋር ያለውን ዝምድና የተመለከተ ጥናት ደግሞ በአሜሪካ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተካሂዷል።
በጥናቱ ታዲያ ተማሪዎች የትምህርት አቀባበላቸውንም ሆነ ያላቸውን ነገር እንዲገልጹ ተደርጎ በርካቶች ራሳቸውን በተለያዩ መንገድ ገልጸዋል።
እውነታው ምንም ቢሆን ተማሪዎች ራሳቸውን የገለጹበት መንገድ የተቃራኒ ጾታዎችን ትኩረት ስቧል።
አንዳንዶቹ ራሳቸውን ከፍ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ትዕቢት እና ጉራ ሳይጨምሩ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ገልጸዋል።
በጥናቱ የተካተቱት ወጣቶች ታዲያ ራሳቸውን ሳይክቡ ዝቅ ብለው ራሳቸውን የገለጹትን አብረን ብንጣመር ደስተኛ ነኝ የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።
ይህ ሁኔታ ከፍ ሲልም ይታያልና፥ ትሁት የሆነን ሰው የግሌ ባደርግ እመርጣለሁም ብለዋል ወጣቶቹ።
በፖለቲካ አስተሳሰብ መቃረን፦ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው አመት ማብቂያ ላይ የተደረገው ጥናት የሰዎች ፖለቲካዊ አመለካከት ተፈላጊነታቸው ላይ ተጽእኖን ያሳድራል ይላል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በ2012 በተካሄደው ምርጫ ላይ በመራጭነት የተሳተፉ ወጣቶችን ምርጫ ለጥናቱ ተጠቅመዋል።
በዚህም በምርጫው ኦባማን የመረጡት ሴቶች በሚት ሩምኒ ደጋፊዎች ዘንድ ተፈላጊነታቸው ዝቅ ያለ ሲሆን፥ በወንዶችም ይኼው ተስተውሏል።
ይህ ደግሞ የሰዎች ፖለቲካዊ አመለካከት መለያየት በአንድ አብሮ ለመዝለቅ የራሱ አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የጥናት ውጤቱ ይገልጻል።
ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ለምርጫ የቀረቡትን ሰዎች ከፖለቲካ አመለካከት አንጻር አጋር ማድረግ ባይፈልጉም በአካላዊ ቁመና ተመራጭ እና ተፈላጊ መሆናቸውን ግን አልካዱም።
አቀማመጥም ሌላው ተፈላጊነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ የማሳረፍ አቅም አለው ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
እጅ በደረት አድርጎ መቀመጥና ትንሽ ዘና ብሎ መቀመጥን የሚያዘውትሩት ሰዎች፥ በተቃራኒ ጾታዎቻቸው የተለያየ ተፈላጊነት መጠን እንዳላቸው በመጥቀስ።
ዘና ብለው መቀመጥን የሚያዘወትሩት የሰዎችን ትኩረት የሚስቡና በሁለቱም ጾታዎች ዘንድ ተፈላጊ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ከላይ የተጠቀሱት የሰዎች የተፈላጊነት እና ተመራጭነት ሁኔታ ላይ ተጽእኖ የማሳረፍ አቅም ያላቸው ተብለው የተገለጹ ሲሆን፥ ተመራማሪዎቹ ከዚህ ጋር የተያያዙ ሰፊ ጥናቶችን እያደረጉ ነው።
ምንጭ፦ independent.co.uk