በጀርመን መዲና በርሊን የሚገኘው ቦዴ ሙዚዬም 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የወርቅ ሳንቲም መዘረፉ ተሰምቷል።
የበርሊን ፖሊስ እንዳለው ዘራፊዎች ወደ ሙዚየሙ ዘልቀው በመግባት 100 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን የወርቅ ሳንቲም ሰርቀው ተሰውረዋል።
“big maple leaf” በመባል የሚታወቀው ግዙፉ ሳንቲም 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ እንዳለው ቢታተምበትም 100 ኪሎ ግራም ንፁህ 24 ካራት ወርቅ በመሆኑ በአሜሪካ ገበያ 4 ሚሊየን ዶላር ያወጣል ተብሏል።
ዘራፊዎቹ በምሽት በሙዚዬሙ መስኮት በኩል በመግባት ሳንቲሙ የተቀመጠበትን ሳጥን በመሰባበር ውዱን ሳንቲም ዘርፈዋል፤ ፖሊስ ከመድረሱ በፊትም ከአካባቢው ተሰውረዋል ነው ያሉት የሙዚየሙ ቃል አቀባይ ስቴፈን ፒተርሰን።
ሶስት ሴንቲሜትር ውፍረት እና 53 ሴንቲሜትር ዲያሜትር ያለው የወርቅ ሳንቲሙ በፊት ገፁ የንግስት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ ምስል በጀርባው ደግሞ የማፕል ቅጠል ምስል አርፎበታል።
ይህ ውድ የወርቅ ሳንቲም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 የተቀረፀ ሲሆን፥ በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ስሙ መስፈሩ ተገልጿል።
የቦዴ ሙዚየም እስካሁን የጠፋውን ሳንቲም ባለቤት አልገለፀም።
በአለማችን ከፍተኛ መጠን ያለው የሳንቲም አይነቶችን የያዘው የቦዴ ሙዚዬም፥ የጠፋው ሳንቲም ከ2010 ጀምሮ በውሰት ተቀብሎ አስቀምጦት እንደነበር በድረ ገፁ ላይ አስነብቧል።
ምንጭ፦ www.cbc.ca/