ስሙኝማ…በደስተኝነት ከዓለም 119ኛ ሆንን! ይቺን ይቺንማ ዝም ብለን አናልፍም፡ ልክ ነዋ… ከፈለገ ‘ኤይድ’ ምናምን የሚሉት ነገራቸው ይቀራል እንጂ እንዲህማ ‘ለፍቶ መና’ አያደርጉንም!
እናማ…እኛ በጣም ‘ደስተኞች’ መሆናችንን ዓለም እንዲያውቅልን መከራችንን እያየን፣ እዛ ታች አውርደው የሚፈጠፍጡን ለምንድነው! የፈረንጅ ምቁነት የሚያበቃው መቼ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
ቆይማ…የሌሊቱ ሰዓት አልበቃ እያለን ቀኑን ሙሉ የቡና ቤቶችን ውስጥና በረንዳ ሳይቀር እያጨናነቅን የምንውለው ‘ቢከፋን’ ነው! እግራችንን ሰቅለን ‘ሲፕ’ ከማድረግ የባሰ ምን ደስተኝነት አለ!
እነሱ እንደየ አገራቸው ስርአት ዳንስ ቤቱና ቡና ቤቱ ሌሊት በስድስትም፣ በስምንትም ሰዓት ይዘጋልና እዚህ ‘የ24 ሰዓት አገልግሎት’ እየተሰጠ… አለ አይደል… እንዴት ነው በደስተኝነት ጭራው አካባቢ ናችሁ የሚሉን!
እኔ የምለው… ይኸው አዳዲሱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሁሉ ዘፈን፣ በዘፈን አድርገነው ውለን እያመሸን “ደስተኛ አይደላችሁም” እያሉ በሞራላችን ‘ቤዝቦል’ የሚጫወቱት ለምንድነው! “ለእኔም አምጪ፣ ለአንቺም ጠጪ…” ከማለት የበለጠ ደስተኝነተ ከየት ልናመጣላቸው ነው! እስቲ አሁን “በቴሌቪዥንና በኤፍ.ኤም ጣቢያዎች በከፍተኛ ደረጃ ዘፈን በማዘፈን ቀዳሚው አገር የትኛው ነው?” የሚል ጥናት ይካሄድና ማን ዓለምን እንደሚመራ ይታይ!
“እኛን በተመለከተ ዓለም ‘ፌይር’ አይደለችም” የሚሉ ወዳጆቻችን ‘እውነት’ ብለዋል፡፡
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በአስደናቂ የጊዜ ፍጥነት ወንዶች ሱሪያችንን ዝቅ፣ ዝቅ… ሴቶች ቀሚሳቸውን ከፍ፣ ከፍ ያደረግነው…‘የደስታችን መጠን’ ጨርቃችንን ሊያስጥለን መድረሱን እንዲያውቁልን አይደል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን… እግረ መንገዴን… የቀሚሱስ ነገር ይሁን ብለን እንለፈው… ለዚህ ሱሪ ዝቅ የማድረግ ነገር…የብቃት ማረጋገጫ ደረጃ እናውጣ እንዴ! ልክ ነዋ…ትልቁም ትንሹም የቀበቶው ዘለበት የተበጠሰበት እየመሰለ፣ ቀበቶ የማሠሪያ ዳርቻን እንደ ፓውንድ አቅም ቁልቁል እያንደረደረ ነገሩን ‘የጋራ’ ካደረግነው…የሆነ ነገር እንጻፍለታ፡፡ “ዕድሜያቸው ከምናምን እስከ ምናምን ላሉ ወንዶች ሱሪ ከተለመደ ማረፊያው ከአምስት ሴንቲ ሜትር ባልበለጠ ዝቅ ማለት ይችላል፡፡ ይህንን መመሪያ ጥሶ የተገኘ ለአንድ ዓመት ተኩል የሱሪው ዳርቻ ደረቱ ላይ እንዲሆን ይደረጋል…” ምናምን አይነት ነገር እንጻፍና ይለይለት፡፡
ስሙኝማ…ወጣቶቹን እያየን፣ “እነኚህ ልጆች ነገ በውስጥ ሱሪ ብቻ መሄድ እንዳይጀምሩና ዓለም ጉድ እንዳይል!” እያልን ስጋት ላይ ባለንበት፣ ይሄ ‘ወይራ፣ ወይራው’ ሁሉ (ቂ…ቂ…ቂ…) የምን ሱሪ ዝቅ ነው! በሚበላው አይስክሪምና ‘በሌላ አይነት አይስክሪም’ ከወጣቶቹ ጋር ፉክክሩ ሳያንስ በሱሪ ዝቅም መጀመሩ ነው!
ነገርዬው ከአፍሪካ አሜሪካውያን የተቀዳ ነው የምንል አለን፡፡ እንደ እውነቱ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ ‘ለመኮረጅ’ ምንም አፍሪካ አሜሪካውያን፣ ጀርመናውያን፣ ሞንጎሊያውያን ማለት አያስፈልግም፡፡ አንድ ሰው ዛሬ ፒያሳ አካባቢ የሆነ አለባበስ ለብሶ ከታየ ልክ… “አዋጅ፣ አዋጅ ስማ ተስማማ…” ምናምን የተባለ ይመስል፣ በአራተኛው ቀን ሙሉ ከተማው ‘ኮርጆ’ ቁጭ ነው፡፡
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ ሱሪ ዝቅ የማድረግ ‘ፋሺን’ ከአፍሪካ አሜሪካውያን ተኮረጀ ቢባል እንኳን… በየክሊፑና በየፊልሙ እንደምናየው ሱሪያቸው ዝቅ ይበል እንጂ ‘ሌላ ለአደባባይ የሚጋለጥ ነገር’ አይተን አናውቅም፡፡ የምር ግን አሁን አሁንማ “ሰዉ ሁሉ ምን ነካው?” ያሰኛል፡፡ አሀ… ጎንበስ በተባለ ቁጥር ዓይናችንን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንድናዞር መገደድ አለብን እንዴ! የፈለገው የሰው ዘር መገኛ ብንሆን…የሉሲ እኮ ‘አጽሟ ብቻ’ ነዋ የታየው! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… ደስተኝነታችንን ለማሳየት መከራችንን እየበላን መቶ ምናምነኛ ያደርጉናል!
እሺ በየጊዜው ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ የሚናገሩት ለምን በቃለ ጉባኤ ምናምን አይያዝልንም! “መንደሩ የሚነሳው በልማት ምክንያት በመሆኑ መደሰታቸውን አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ…” የሚባለው ለምን ‘እንደ መመዘኛ’ አይካተትልንም!
ለነገሩማ…ሹክ የሚል አለ ማለት ነው፡፡ እየሄደ ለ‘ፈረንጆቹ’ “ሁሉም ነገራቸው ውሸት ነው…” እያለ የሚያሳብቅብን አለ ማለት ነው፡፡
“ካሜራ ፊት ደስተኞች መስለው በሆዳቸው… እኛን እንደነቀላችሁን የሚነቅል ይንቀላችሁ!” እያሉ ነው ብሎ የሚያሳብቅ አለ ማለት ነው፡፡
“እኛን በተመለከተ ዓለም ‘ፌይር’ አይደለችም” የሚሉ ወዳጆቻችን ‘እውነት’ አላቸው፡፡
እናማ…በተለመደው የፈረንጅ ‘ተንኮል’ ያልታዩልን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ “ለምን ለጠላት ደስ ይበለው!” እያልን ለቅሷችንን በውስጥ፣ ሳቃችንን በአደባባይ እንደምናደርግ ለምን ነጥብ አያሰጠንም!
“እኛን በተመለከተ ዓለም ‘ፌይር’ አይደለችም” የሚሉ ወዳጆቻችን ‘እውነት’ አላቸው፡፡
የምንበላው በቂ ምግብ እንኳን ባይኖረንም ደህና ለብሰን፣ ደህና ተቀባብተን አደባባይ የምንወጣው ‘ደስ’ ቢለን አይደል!
“እኛን በተመለከተ ዓለም ‘ፌይር’ አይደለችም” የሚሉ ወዳጆቻችን ‘እውነት’ ብለዋል፡፡
በየስብሰባ አዳራሹ ደህና ሊጠፉ ነው የተባሉ እነ ልብ ድካምና፣ ሪህን ለሚቀሰቅሱ ንግግሮች ጣራው እስኪነቃነቅ የምናጨበጭበው ‘ደስተኝነታችን’ በቴሌቪዥን ይታይልናል ብለን አይደል እንዴ! ‘መዳፋችን ሲላጥ የከረመው’ ከፍቷችኋል ለመባል እንዳልሆነ ልብ ይባልልንማ፡፡
የከተማውን ካፌዎች ጢም አድርገን እየዋልን፣ ዓለም ደስተኝነታችንን እያየልን ነው ስንል ለካስ ‘ሲደገስልን’ ከርሟል! በደስተኝነት ‘ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሦስተኛ’ ምናምን እንባላለን ስንል እንዲህማ ኩም አያደርጉንም፡፡
“እኛን በተመለከተ ዓለም ‘ፌይር’ አይደለችም” የሚሉ ወዳጆቻችን ‘እውነት’ አላቸው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የደስተኝነት ነገር ካነሳን አይቀር…አንዳንዱ ሰው ግርም አይላችሁም!… አሮስቶ ዲቤቴሎውን በሬሚ ማርቲን እያወራረደ … “አሁን ይሄ አገር ነው!” የሚል ሰው ለምን ሪያሊቲ ሾው ምናምን አይጀምርም! ጉደኛ ‘በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ’ ትወና ነዋ!
ውስኪ በመለኪያ ሀያ፣ ሠላሳ ምናምን ብር ሲገባ… “አሁንስ የት አገር እንሰደድ!” የሚሉ ሰዎች መሆን አለባቸው ደስተኞች አይደሉም ያሰኙን፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… “ነገርኳችሁ፣ ይቺ አገር ተስፋ የላትም፡፡ ውስኪ ዛሬ እንዲህ የሆነ ትንሽ ቆይቶ እኮ ለዓይናችንም ልናጣው ነው!” ይልላችኋል፡፡ (ሌላው ደግሞ አስራ ሦስት ቀን ድስት ውስጥ መሽጋ የከረመች ሹሮውን እየበላ… “ተመስገን ነው፣ ይህንን ማን አየብኝ!” የሚባልባት አገር እንደሆነች ይመዝገብልን፡፡
እናማ… ጥያቄ አለን… ያኔ የኳሱ ጊዜ እንደዛ ‘ጥግ ድረስ የተደሰትንበት’ አልተያዘልንም ማለት ነው! “ከ31 ዓመት በሁዋላ…” ስንል የከረምነው እኮ ‘የደስታዎች ሁሉ እናት’ ምናምን ተብሎ እንዲመዘገብልን ነበር! በውድድሩ ውራ ሆነን እንጨርሳ! ውራነተ ለእኛ ብርቃችን ነው እንዴ! የጎል ዕዳ ተሸክመን እንመለሳ! እንኳን የኳስ ቡድን…አለ አይደል…አገር ስንት ዕዳ አለባት አይደል እንዴ! (ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ ከለመድነው አንዲት ዶላር ይቀንሱብንና …መቆራረጫችን ይሆናል፡፡ “መቃብራችን ላይ እንዳትቆም!” ምናምን ለመባባል ባንችልም…ዕድሜ አተላ ብቻ ለቀረበት የቡና ስኒ! ቂ…ቂ…ቂ… )
“እኛን በተመለከተ ዓለም ‘ፌይር’ አይደለችም” የሚሉ ወዳጆቻችን ‘እውነት’ አላቸው፡፡
መሄዴ ነው መልቀቄ ነው ከአገር
እንቅቡም ሰፌዱም ነካካኝ በነገር
ተብሏል፡፡ እኛ ለ‘ሚድል ኢንካም’ እየተሟሟትን “ደስተኞች አይደላችሁም” እያሉ አይነካኩና፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!