ማለዳ ተነስተው የመኪናቸውን ጎማ እየቀየሩ ነበር፡፡ ቀድሞውንም ብዙ የማይግባቡዋት ጎረቤታቸው አጠገባቸው መጥታ ምራቅ እንደተፋች ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም በአፀፋው ሰው ፊት ምራቅ እንዲህ አይተፋም ብለዋል፡፡ ይህን ጊዜ ግን ዳግም መናገር የማይፈልጉትን ስድብ ትሰድባቸዋለች፡፡ እሳቸውም በአፀፋው በራሷ ሳይሆን በሰዎች እርጥባን እንደምትተዳደር አድርገው ይሰድቧታል፡፡ ሴትዮዋ የዛኑ ዕለት ፖሊስ ጣቢያ ሄዳ ሰድቦኛል፣ ክብሬ ተዋርዷል ብላ ትከሳለች፡፡ ከፖሊስ ጣቢያ መጥሪያ ይደርሳቸውና በተጠሩበት ቀን ይቀርባሉ፡፡ ፖሊስ ጣቢያ የተጠሩበትን ምክንያት መርማሪ ፖሊሱ አስረድቶ በእሳቸው በኩል ያለውን ይጠይቃቸዋል፡፡ እሳቸውም ስትሰድባቸው መሳደባቸውን ይናገራሉ፡፡ ግጭታችሁን በእርቅ ፍቱ የሚል ሐሳብ በፖሊሱ ሲቀርብ እሳቸው እርቁም ክሱም ይመቸኛል ቢሉም ሴቲቷ ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ በዚህም ምክንያት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ በፍርድ ቤት ክሱ ተነቦላቸው የሚሰጡት አስተያየት ካለ ሲጠየቁም፣ ስትሰድበኝ ከቁጥጥር ውጭ ሆኜ ሰድቤያታለሁ ማለታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ለዚህም የ70 ብር ቅጣት ተጥሎባቸው እንደተሰናበቱ ይናገራሉ፡፡
በከተማም ሆነ በገጠር ስድብ ምርቃት እስኪመስል ድረስ መሰማቱ የተለመደ ነው፡፡ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በትራንስፖርት፣ በገበያ ሥፍራ፣ በጎዳና አልፎ አልፎም በቤተ እምነት አካባቢ እንኳን ሳይቀር ሰዎች ሲሰዳደቡ ይሰማል፡፡ በተለይ በጉዳዩ ውስጥ ካሉ ወገኖች አልፎ የእናትን ወይም የቤተሰብን ክብር የሚነካ ፀያፍ ስድብም በየጊዜው መሰማቱ አልቀረም፡፡
ለምን ይሳደባሉ?
አንዱ ሌላውን እንዲሰድብ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በስድብ መድረክ የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ ሳይኮሎጅ ቱዴይ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ ሆኖም ፆታ፣ ዘርና ሃይማኖት እንዲሁም ዕድሜ ሳይለይ ብዙዎች ይሳደባሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ለራሳቸው ደኅንነት የለንም ብለው ሲያስቡ ነው፡፡ ሌሎችን በመሳደብ የራሳቸውን ደኅንነት ያስጠበቁም ይመስላቸዋል፡፡ ስለራሳቸው ጉዳይ ሌሎች ትኩረት እንዲሰጡላቸውም ይሳደባሉ፡፡ ሰዎች ሲናደዱ ስድብ የሚሰነዝሩትም በተቃራኒ ወገን በኩል የተነሱ ጉዳዮችን በንግግር መፍታት ስለማይችሉ ነው፡፡ ሁል ጊዜም የሚሳደቡት ተቃራኒውን ወገን ጥፋተኛ አድርገው ሲሆን፣ ከራሳቸው በኩል ያለውን ክፍተት ግን ማየት የማይችሉም ናቸው፡፡ ለተፈጠረው ነገር መፍትሔ፣ ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅም በስድብ ላይ ስድብ የሚያወርዱ አሉ፡፡ ታዲያ ለክስተቶች የስድብ ምላሽ የሚሰጡት፣ የበሰሉ ሰዎች አይደሉም፡፡
የበሰሉ ሰዎች ሌሎችን ሳይሳደቡ መግባባትና መነጋገር ይችላሉ፡፡ ሁሉንም ጉዳይ ከራሳቸው ፍላጎት አንፃር አያያይዙትም፡፡ የሌሎችን ያከብራሉ፣ ሐሳባቸውንም ያዳምጣሉ፡፡ በሐሳቡና በድርጊቱ ባይስማሙም፣ ሁኔታውን ሙያዊ በሆነ ንግግር ያልፉታል፡፡ ስድብ ማንም የማያሸንፍበት መድረክ መሆኑንም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ይቀርና ግን ስድብ ሌላ መዘዝ ያስከትላል፡፡
በአንድ የግል መሥሪያ ቤት በኃላፊነት ደረጃ የሚሠሩ ባለሙያ እንዳጫወቱን፣ ሥራ ላይ እያሉ ከሌላ ባልደረባቸው ጋር መግባባት አልቻሉም፡፡ ብዙ ጊዜም በሥራ ባልደረባቸው ሥራቸውን ከመሥራት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ስድቦች ደርሶባቸዋል፡፡ አንድ ቀን ግን ሁኔታውን እንዲሁ ተሰድበው ብቻ አላለፉትም፡፡ እንደሚያስታውሱትም፣ የሥራ ባልደረባቸው ከሳቸው አልፈው እናታቸውን በስድብ መልክ በማንሳት አንተን ብሎ የሒሳብ ባለሙያ ይላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ እጃቸውን እንዴት እንደሰነዘሩት አያስታውሱም፡፡ የሰነዘሩት ቦክስም ያረፈው የተሳዳቢው ጥርሶች ላይ ነበር፡፡ በዚህም የፊት ሁለት ጥርሶቻቸው ይወልቃሉ፡፡ ጥርሳቸው የወለቀባቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ለመውሰድ ፈልገው የነበረ ቢሆንም፣ እዛው ቢሮ ውስጥ ባሉ ሠራተኞች አማካይነት እርቅ ተፈጥሮ፣ ተማች ባልደረባቸውን እንዲያሳክሙ ተደርጓል፡፡
በተሳዳቢና ተሰዳቢ መሀል ሁልጊዜም ጉዳዮች በእርቅ አያልቁም፡፡ ለድብድብና ለጉዳት ሲዳርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ በከተማዋ በአንዳንድ ታክሲ ረዳቶችና ተሳፋሪዎች፣ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በገበያ ሥፍራዎችና በጎዳና ሲከሰትም ይታያል፡፡
በአንድ የግል መሥሪያ ቤት በሾፌርነት ከመቀጠሩ በፊት የታክሲ አሽከርካሪ እንደነበር የነገረን ወጣት፣ በታክሲ ፊርማታዎች አካባቢ የሚነገር የስድብ ዓይነት አፀያፊና የሚዘገንን ነው ይላል፡፡ ‹‹ታክሲ ላይ የተቀመጠ ተሳፋሪ ዕድሜና ፆታ ሳይለየው ሲሳደብ ይሰማል፡፡ የረዳቶች ባህሪ እንዳለ ሆኖ ከረዳቶች ጋር ተግባብቶ መሳፈር የሚችለው ጥቂቱ ነው፡፡ ታክሲ ውስጥ ስድብ ለመሰዳደብ አምስት ሳንቲም መልስ አለመስጠት በቂ ነው፤›› ሲልም ያክላል፡፡
መነሻውን ከፒያሳ አድርጎ በሚሠራበት ወቅት ብዙ የሚያውቃቸው አሽከርካሪዎች፣ ረዳቶች እንዲሁም ተሳፋሪዎች ተሰዳድበው ጉዳዩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄድ ይመለከት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
ክብር የሚነኩባቸው መንገዶች
ክብር የሚነኩባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ ከክብር ጋር የተያያዙ ወንጀሎችም በሦስት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ስም በማጥፋት፣ ሁለተኛው በሐሴት ሀሜት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ በስድብ ነው፡፡
በማናቸውም ፍርድ ቤት የሕግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም የችሎት የቴሌቪዥን ድራማ ፕሮግራም የሕግ ጽሑፍ አዘጋጅና ተዋናይ ሙሉጌታ በላይ እንደሚሉት፣ ስም ማጥፋት የሚባለው አንድ ሰው ስሙን ሊያጠፋና ሊያሰድበው የሚችል የተፈጥሮ ወይም ራሱ ያመጣው ገድለት ሲኖረው ነው፡፡ ሰዎች ይህ እውነት የሆነውን ነገር ይዘው እሱ እንደዚህ ነው እያሉ ስም ሲያጠፉ ስም ማጥፋት ይባላል፡፡ ብዙውን ጊዜ በቀጥታ ለባለቤቱ የሚነገር ሳይሆን፣ ለሦስተኛ ወገን የሚነገርም ነው፡፡
የሐሴት ሀሜት የሚባለው ሰው ጋር የሌለን ወይም ያልሆነን ነገር አለ ብሎ ክብር መንካትና ማዋረድ ነው፡፡ ይህም በሌላ ወገን አንድ ሰው የሌለውን ወይም ያልሆነውን አለው ወይም ሆኗል ብሎ በሐሰት መናገር ነው፡፡
ስድብ ሦስተኛው ሲሆን፣ ከስም ማጥፋትና ከሐሴት ሐሜት የሚለው በእውነት ወይም በውሸት ላይ ተመሥርቶ በአካል እንቅስቃሴ ወይም በቃል በቀጥታ ለባለቤቱ የሚባል በመሆኑ ነው፡፡
ቅጣቱ ምንድን ነው?
ከስም ማጥፋት ጋር የተያያዘው ከስድስት ወር ባልበለጠ እስራት ወይም በመቀጮ (በገንዘብ) ያስቀጣል፡፡ በኢትዮጵያ ቀላል እስራት ማለት ከአሥር ቀን እስከ ሦስት ዓመት ሲሆን፣ የገንዘብ ከአሥር ብር እስከ 10,000 ብር ድረስ ነው፡፡
የሐሴት ሐሜት ከሆነ ከአንድ ወር በማያንስ ቀላል እስራት ሲያስቀጣ፣ እንደ ክብደቱ እስከ ሦስት ዓመት ሊሄድ ይችላል፡፡
ስድብ ሲታይ በቃል ብቻ የሚባል አይደለም፡፡ በአሽሙርና በምልክት ስድብ አለ፡፡ ሰውን የሚያዋርድና የሚጎዳ ስድብም አለ፡፡ ይህ ከአሥር ቀን ጀምሮ ከሦስት ወር በማይበልጥ እስራት ወይም በመቀጮ ያስቀጣል፡፡
እንደ አቶ ሙሉጌታ፣ ከሌሎች ወንጀሎች በተለየ ሁኔታ ሕጉ ላይ የተቀመጠ ነገር ግን ብዙ ጊዜ በፍርድ ቤቶችና በባለሙያዎች ትዝ የማይባል ጉዳይ አለ፡፡ ይህም የግል ተበዳዩ (የተሰደበው) ተናዶ መልሶ ሲሳደብ፣ ሕጉ ያስቀመጠውን ችላ ማለት ነው፡፡ ሕጉ ሁለት አማራጮች አስቀምጧል፡፡
አንደኛው በከሰሰበት ጉዳይ ከሳሽን ጨምሮ ሁለቱም የሚጠየቁበት ወይም ሁኔታውን ዓይቶ አንዱን ጥፋተኛ የሚልበት ነው፡፡ ሌላው ምናልባት ተሳዳቢው፣ በዛኛው ወገን በጣም ክብርን የሚነካ አፀያፊ ስድብ ተሰድቦ ከሆነና ሌላም ሰው በዚህ መልኩ ቢሰደብ አፀፋ ይሰጣል ብሎ ፍርድ ቤቱ ሲያምንና በአንደኛው ወገን ማነሳሳት ከነበረ ፍርድ ቤቱ እንደ ቅጣት ማቅለያ ዓይቶ በነፃ ሊለቀቅ ይችላል፡፡
ክብርን የመንካት ወንጀል ሁልጊዜም በግለሰቦች ላይ ብቻ የሚፈጸም አይደለም፡፡ ቅጣቱን የሚያከብዱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በመንግሥት ሠራተኛ ላይ ከሆነ በተለይ የመንግሥት ሥራውን በሚሠራበት ሰዓት ላይ የስም ማጥፋት፣ የሐሴት ሀሜትና ስድብ ላደረገ ቅጣቱ ከባድ ይሆናል፡፡ ከቢሮ ውጭ ላይ ሆኖም ከመንግሥት ሥራው ጋር በተያያዘ ክብርን የሚነካ ለምሳሌ ከፅዳት ሥራው ጋር አያይዞ የሚሳደብ ሰው ቅጣቱ እንደተራ ወንጀል ቀላል አይደለም፡፡ ከስድስት ወር በማያንስ እስራት እና ከ1,000 ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
ሰው ቢሰድበኝ ለስድብ ፍርድ ቤት እሄዳለሁ ወይ? ብለው ራሳቸውን ከሚጠይቁ ሰዎች አንዱ ጠበቃ ሙሉጌታ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት የሚያቀኑት ለራሳቸው ከሚሰጡት ክብርና ለነገሮች እንደሚሰጡት ክብደት ይወሰናል፡፡ ሆኖም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችንና ፖሊስ ጣቢያዎችን ከሚያጨናንቁ ጉዳዮች አንዱ ከክብር መነካት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ተሰደብኩ፣ ተዋረድኩ እንዲሁም ስሜ ጠፋ ብለው የሚያመለክቱም ብዙ ናቸው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በነበሩበት ጊዜ ከሚሠሯቸው ከአሥር መዝገቦች ውስጥ እስከ አራት የስድብ የሚሆንበት አጋጣሚም ነበር፡፡
‹‹በየዕለቱ ኑሮዋችን ከምናየውና ከምንሰማው ክብርን የሚነኩ ስድቦች፣ የስም ማጥፋትና የሐሴት ሀሜቶች አንፃር የሚመጡት ጥቂት ናቸው ሊባል ይችላል፡፡ ሰው ሲበደል ይሳደባል፣ አገልግሎት በደንብ ሳያገኝ ሲቀር ይሳደባል፣ የሚከበርና በመንደሩ መልካም የተባለ ግለሰብ መኪና ይዞ መንገድ ላይ እግረኛ ወይም መኪና ያላግባብ ሲገባበት ሲሳደብ ይሰማል፡፡ በየደቂቃው የሚሰሙ ከመሆናቸው አንፃር ብዙው ወደ ሕግ አይሄድም፡፡ ስድቡን በስድብ አፀፋ መመለስን ይመርጣል፤›› ይላሉ፡፡
እናትህን —– ላድርግ ብለው ከግለሰቡ አልፈው ቤተሰቡ ላይ የሚሄዱ ስድቦች ደግሞ ብዙ ጊዜ ለግጭት መነሻ ናቸው፡፡
የስድብ ተፅዕኖ
በሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ አንዱ አንዱ ላይ አዎንታዊ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን መስጠት ለሥራ ያነሳሳል፣ በራስ መተማመንን ያጎለብታል፡፡ ስድብ ደግሞ የዚህ እኩል የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡትን ግምትና መተማመን ያሳጣል፡፡
በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህሩ አቶ እስጢፋኖች አበራ እንዳብራሩት፣ አሉታዊ የሆኑ አስተያየቶ የሰዎችን ቅስም ይሰብራሉ፡፡ ይህ በሕፃናት ላይ ሲሆን ጉዳቱ ያመዝናል፡፡
ስድብ ወይም አሉታዊ አስተያየቶች ሰዎች ከማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዲቆጠቡ፣ እንዲገለሉ ከዚህ ሲያልፍም ሌሎችን ለመጉዳት ወይም ራስን ለማጥፋት እንዲነሳሱ ምክንያት ይሆናል፡፡
ሰደበኝ/ሰደበችኝ በሚል የሚጎዳዱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የሕግ ተጠያቂነት ቢኖርም ስድብ የሰውን ሰብዓዊነት በማጠልሸት ሰዎች በሰው ፊት ለመቆም ድፍረት እንዲያጡም ያደርጋል፡፡
እንደ አቶ እስጢፋኖስ፣ ሰዎችን እንዲሳደቡ የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ እንደ ልማድ ከማድነቅ ይልቅ ለመተቸትና አቃቂር ለማውጣት የሚተጉ መኖራቸው፣ ሕፃናት ሰዎች ሲደናነቁ ሳይሆን ሲሰዳደቡ እያዩ በማደጋቸው፣ ጨለምተኛ ሆነው ዓለምን በአሉታዊ ጎን የሚያዩና ይህን ልማድ ያሳደጉ መኖራቸው እንደ ምክንያት ሊነሱ ይችላሉ፡፡
በየአካባቢው ስድብ ልማድ እየሆነ መምጣቱ፣ ሕፃናትም ይህንን እየሰሙ እያደጉ መሆኑና አስተዳደግና የአካባቢ ተፅዕኖም ተሳዳቢ ሊያደርግ መቻሉንም ይጠቅሳሉ፡፡
ብዙ ጊዜ በአገራችን በጉዳዮች ላይ ጊዜ ወስዶ የመነጋገርና ችግሮችን የመፍታት ክፍተት ለስድብ አንዱ መንስኤ ነው፡፡ በትምህርት ቤትና በመሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ወላጆች በቤት ውስጥ ጉዳዮችን በንግግር ከመፍታት ይልቅ በስድብ መመለስ ይቀናቸዋል፡፡ ይህም ከመፍትሔ ይልቅ ችግር አፈታታችን ላይ ክፍተት ይፈጥራል፡፡
የግጭት አፈታትና የንግግር ባህላችን ደካማ መሆን ሰዎች ቶሎ ስሜታማ ሆነው የስድብ አዙሪት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚያደርግም አቶ እስጢፋኖስ ያክላሉ፡፡
ስድብ በየጊዜው ከመሰማቱ አንፃር የተለመደ ቢመስልም ለሥነ ምግባር ጉድለት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የሰውን ስብዕና በቃላትና በድርጊት ማዋረድ ከሥነ ምግባር አንፃር እንደ ትልቅ ችግርም ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም የሥነ ምግባር መገለጫው ሌሎችን ከማክበርና በጉዳዮች ላይ በመነጋገር የሚጀምር በመሆኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ እንደሚሉትም፣ የሰው ልጅ ክብሩ ሳይጓደልበት እንዲኖር፣ የሌሎችን ክብር መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ሰዎች እንዲሸማቀቁ ማድረግም ከሃይማኖት አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡ በመሆኑም ያጠፋ ሰው ቢኖር ይመከራል፣ ይገሰፃል፡፡ ክብሩ እንዲገፋፉና እንዲዋረድም አይፈቀድም፡፡