ቸል የተባሉ የትሮፒካል በሽታዎችን ለማከም የተደረገው የመድሃኒት ስርጭት ስኬታማ መሆኑን ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አስታወቀ፡፡
የትሮፒካል በሽታዎች ከሚባሉት ትራኮማ፣የስጋ ደዌ በሽታ፣የጊኒዎርም፣የእብድ ውሻ በሽታና ዝሆኔ(lymphatic filariasis) ይጠቀሳሉ፡፡
መድሃኒቶቹን የማድረስ ጥረት የተጠናከረው ከአምስት አመት በፊት ለንደን ላይ ከተካሄደው ወሳኝ ጉባኤ በኋላ መሆኑም ተመልክቷል ፡፡
በ2015 በአለም አቀፍ ደረጃ አንድ ቢሊየን ያህል ሰዎች ቢያንስ አንድ የትሮፒካል በሽታ ህክምና አድርገዋል ፤ካምፓኒዎችም ከ2012 ጀምሮ ሰባት ቢሊየን ያህል መድሃኒቶችን አሰራጭተዋል ፡፡
የውሃንና የንፅህና አቅርቦትን በማሻሻል የበለጠ ውጤት ማግኘት እንደሚቻልም የአለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የለንደኑ ጉባኤ ቸል የተባሉ 10 የትሮፒካል በሽታዎችን ለመቆጣጠር አልያም ለማስወገድ ቃል የተገባበት ነበር ፤ከነዚህም እኤአ በ2020 ጊኒ ዎርም ፣ሪቨር ብላይንድነስ እና ትራኮማን ለማጥፋት ያለመ ነው ፡፡
170 ሺህ ያህል ሰዎች በየአመቱ ከህመሞቹ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሲሆን በሽታዎቹ የበለጠ ተፅእኖ እየፈጠሩ ያሉት በሽተኞቹን የአካል ጉዳት በማድረስ ማሰቃየታቸው ነው ፡፡
ቢል ጌትስ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት “የመድሃኒት አቅራቢ ተቋማትን በመደገፍ በሽታዎቹን በመከላከል የድርሻቸውን እንዲወጡ እናደርጋለን ህክምናውም በስፋት እንዲሰጥ ይሆናል” ብለዋል ፡፡