) በየቀኑ ስራችንን ለማከናወን ከምንጠቀመው እያንዳንዱ ጊዜ ውስጥ 5 ደቂቃ በመመደብ ጤናማ እና ደስተኛ የሚያደርጉ ጠቃሚ ነገሮችን ማግኘት እንችላለን።
እነዚህ በየቀኑ የሚመደቡ 5 ደቂቃዎች ለሰዎች ስለሚሰጧቸው የደስታና የጤና ጥቅሞች በምርምር የተደገፉ መረጃዎች ቀርበዋል፡፡
1. በየቀኑ ለአምስት ደቂቃ መሮጥ በህይወት መኖርን በሶስት ዓመት ይጨምራል፡፡
በየቀኑ ለአምስት ደቂቃ መሮጥ አስቀድሞ የመሞት እድልን በመቀነስ የመኖር እድልን ይጨምራል፡፡
በ55 ሺህ ወንዶች እና ሴቶች የተጠና ጥናት በየቀኑ የሚሮጡ ሰዎች ከማይሮጡት በአማካይ 30 በመቶ የመሞት እድላቸውን ይቀንሳሉ፡፡
ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸውም የሚሮጡት ሰዎች ከማይሮጡት በ45 በመቶ ዝቅ ያለ ነው ብሏል ጥናቱ፡፡
የሚያጨሱ እና ክብደታቸው የጨመሩ ሰዎችም በየቀኑ አምስት ደቂቃ ቢሮጡ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
በርካታ ጥናቶች እንደሚሉት አነሰም አደገም በየቀኑ መሮጥ የጤና ጥቅሙ ከፍተኛ ሲሆን፥ አዛውንቶች ለ15 ደቂቃ ያህል እርምጃ ቢራመዱ 20 በመቶ የመሞት እድላቸው ይቀንሳል፡፡
2. በስራ ቦታ አካባቢ በየሰዓቱ ለአምስት ደቂቃ መንቀሳቀስ ድብርትን ያስወግዳል፤ ጤናማ ያደርጋል፡፡
ብዙ ጊዜ ተቀምጠው የሚያሳልፉ ሰዎች ለውፍረት፣ ለስኳር በሽታ እና ሌሎችም በመቀመጥ ብዛት ለሚመጡ የጤና ቀውሶች ይጋለጣሉ፡፡
በስራ ሰዓት ሁሉ ባሉት ጊዜያት ለአምስት ደቂቃ መንቀሳቀስ ድብርትን ያስወግዳል፣ ድካምን በማስወገድ ብርታትን መጨመርና ሌሎችም አዕምሯዊ ጥቅሞች አሉት ተብሏል፡፡
3. ስራን ከተቀመጠው ጊዜ አምስት ደቂቃ ቀድሞ መጨረስ እና አለማዘግየት
ሰዎች በየቀኑ መስራት የሚገባቸውን ስራ ከማዘግየት ይልቅ የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠው ማጠናቀቅ ከሚገባቸው ጊዜ አምስት ደቂቃ በፊት ለመጨረስ ቢሞክሩ ደስተኛ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ይላል የስነ ልቦና ባለሙያው ዊሊያም ጀምስ፡፡
ባለሙያው ስራው ካላለቀም ከመደበኛ ጊዜ በተጨማሪ ከአምስት ደቂቃ በላይ መስራት እንደማይገባም ይመክራል፡፡
ከዚያም እረፍት አድርጎ እንደገና ለመጨረስ መመኮር እንጅ ድካም እስኪፈጥር ድረስ በስራው ላይ ማተኮር ትርፉ ጤናን ማቃወስ ነው ብሏል።
4. በስራ መካከል ለአምስት ደቂቃ እረፍት ማድረግ ፈጠራን፣ ውጤታማነትን እና ተነሳሽነትን ይጨምራል፡፡
በየቀኑ በምንሰራው ስራ ቢያንስ በየሰዓቱ የአምስት ደቂቃ እረፍት መውሰድ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡
በተለይም ተማሪዎች ለ25 ደቂቃ አጥንተው አምስት ደቂቃ ቢያርፉ መልካም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
እረፍት ማድረጋቸው የሚያነቡትን ርእሰ ጉዳይ እንዲረዱትና እንዳይሰለቹ ያደርጋቸዋል፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ አዕምሮ ለብርካታ ሰዓት በአንድ ጉዳይ ላይ በዘላቂ የትኩረት መጠን አይቆይም፤ የራሱ የሆነ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ስላለ እረፍት እና መታደስ ያስፈልገዋል፡፡
5. በየቀኑ በጎ ስለማድረግ፣ ስለደስተኛ መሆን እና ይቅር ባይነት ለአምስት ደቂቃዎች ማሰብ እና በተግባርም መግለፅ ለጤና ይጠቅማል፡፡
በተለይም አዕምሯዊ እርካታን በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ነው ጥናቶች የሚሳዩት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለቤተሰብ፣ ለባል ወይም ለሚስት፣ ለልጆች በትንሹ አምስት ደቂቃ መመደብ ግንኙነትን በእጅጉ ያዳብራል፡፡
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በየቀኑ እና በየሰዓቱ አምስት ደቂቃ እየመደቡ እውን ማድረግ፥ የአዕምሮና የልብ ጤናን ይጨምራሉ፤
ማህበራዊ ግንኙነትን እና በስራ ስኬታማ መሆንን ያመጣሉ፡፡
ምንጭ፡-ሳይኮሎጂ ቱደይ